የ “ባልበላውም ጭሬ ልበትነው” ፖለቲካ አዲስ አበባ፣ #የመገንጠል ጥያቄና የአገር ህልውና ፈተና-ልደቱ አያሌው
Edited by : addiskignit@gmail.com -3/29/2023
የ “ባልበላውም ጭሬ ልበትነው” ፖለቲካ አዲስ አበባ፣ #የመገንጠል ጥያቄና የአገር ህልውና ፈተና #መንደርደሪያ የኢትዮጵያውያን የትስስር ዋና ቋጠሮ የሆነችው አዲስ አበባ የለዬለት ቀውስ ውስጥ ገብታለች ባይባልም በዙሪያዋ አደገኛ ስጋቶች ማንዣበብ ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ አዲስ አበባን ከህልውና አደጋ ለመታደግ እስካሁን ስለተደረገው ትግል ስናስብ የሁለት ፓርቲዎችን ቀዳሚ ሚና እውቅና መስጠት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ለአዲስ አበባ ህልውና መከበር ትኩረት ሰጥተው የታገሉ ናቸው፡፡ አንዳንድ ግለሰቦችና መገናኛ ብዙሃን የነበራቸው አስተዋጽኦም መረሳት የሚገባው አይደለም፡፡ ይሁንና እኔው ራሴ አባል የነበርኩበትና በቅርበት የማውቀው ኢዴፓ ያበረከተውን አስተዋፅኦ በአጭሩ ለዚህ ጽሁፍ እንደ መንደርደሪያነት ለመጠቀም ልሞክር፡፡ #ኢዴፓ 1992 ዓ ም ላይ በተካሄደው አገራዊ ምርጫ “ቀዳሚ አጀንዳችን አዲስ አበባን ነፃ ማውጣት ነው” በሚል መሪ ሃሳብ ተወዳድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ 14 የአዲስ አበባ ምክር ቤት መቀመጫዎችን በማሸነፍ አዲስ የሠላማዊ ትግል ተነሳሽነት መፍጠር ችሏል፡፡ 1997 ዓ ም በተካሄደው ምርጫም የቅንጅት የቅድሚያ ትኩረት አዲስ አበባን አሸንፎ መረከብ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ማሳመን ችሏል፡፡ በዚያ ምርጫ ቅንጅት የአዲስ አበባን ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ ሲያሸንፍም ከዚያ ውስጥ አብላጫውን 62% መቀመጫ ያሸነፈው ኢዴፓ ነበር፡፡ ቅንጅት ምርጫውን እንዲያሸንፍ ያስቻለውን የምርጫ ማኒፌስቶ ያዘጋጀውም ኢዴፓ ነበር። በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ቢቀርም ስትራቴጅክ ጠቀሜታውን አስቀድሞ በመገንዘብ ቅንጅት አዲስ አበባ ምክር ቤትን ተረክቦ እንዲያስተዳድር በወቅቱ ኢዴፓ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚው ጎራ የስም ማጥፋት ዘመቻ የጥቃት ሰለባ በመሆን ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በገጠመው የረጅም ጊዜ ውጣውረድ ተስፋ ባለመቁረጥም በቅርቡ በ2013 ዓ ም ምርጫ ጭምር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተባብረው እንዲወዳደሩና አዲስ አበባን ከገዥው ፓርቲ እንደገና መንጠቅ እንዲችሉ ኢዴፓ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ይሁንና ሌሎች ፓርቲዎች ሊቀበሉት ስላልቻሉ ጥረቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በመጨረሻም ኢዴፓ በምርጫው ቢሳተፍ አዲስ አበባ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅዕኖ በመስጋት በህገ-ወጥ መንገድ ከፓርቲነት እንዲሰረዝና ከፖለቲካ ትግሉ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡ #ኢዴፓ ከጅምሩ በዚህ መጠን ለአዲስ አበባ ልዩ ትኩረት በመስጠት መታገል የመረጠው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ በዋናነት በሚከተሉት ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች ነበር፡፡ አንደኛ፡-ራሱን በኢትዮጵያውያን ማንነት የሚገልፅ በርካታ ህዝብ በሚኖርባት አዲስ አበባ ብሔርተኛ የሆነውን ኢህአዴግን በምርጫ በቀላሉ የማሸነፍ ዕድል መኖሩን በማመን፣ #ሁለተኛ፡-አዲስ አበባ ከተማን አሸንፎ መያዝም በአገር ደረጃ ሠላማዊ ትግሉን የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል እንደ ዋና መደላድል /spring board/ ሊጠቅም እንደሚችል በመገንዘብ፣ ሦስተኛ፡- የብሔርተኝነት ፖለቲካው ወደ ፊት አገሪቱን የማፍረስ ውጤት እንዳያስከትል አዲስአበባ ከተማ ዋና የመከላከያ ምሽጋችን ሆና ታገለግላለች የሚል ስትራቴጅካዊ ግምገማ ስለነበረው ነው፡፡ ይሁንና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በ32 ዓመታት የትግል ጉዟችን ቢያንስ አዲስ አበባ ከተማን አሸንፈን አለመያዛችን አገሪቱን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል፡፡ ለዚህ ሁሉ ዓመታት በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል ያባከነውን ድካም ሁሉ በቅድሚያ አዲስ አበባ ከተማን በምርጫ ለማሸነፍ ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ የዛሬው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በብዙ ርቀት የተሻለና የተለዬ በሆነ ነበር፡ ፡ ወደተሟላ ዴሞክራሲ መግባት ባንችልም እንኳ ወደዚህ ዓይነቱ አስቀያሚ የእርስ በርስ ፍጅት ባልገባን ነበር፡፡ ያለፈው ድክመታችን የሚያስቆጭ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግስት ለማሸነፍም ሆነ የአገሪቱን ህልውና አስጠብቆ ለማስቀጠል በቅድሚያ አዲስ አበባን አሸንፎ መያዝ ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ምትክ-ዬለሽ የሆነ መፍትሄ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህንን መጣጥፍ በአዲስ አበባና በተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ላይ አንድጽፍ ያስገደደኝም ይኸው እውነታነው፡፡ከኛ በላይ የአዲስ አበባከተማን ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታ የተረዳው የወቅቱ አገዛዝከኛ በተሻለ ፍጥነት የሚፈልገውን ሁሉ በህገ-ወጥ መንገድ ጭምር እየሰራ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ነገሮች እንዳይመለሱ ሆነው ከመበላሸታቸው በፊት “በጊዜ የለንም” ፍጥነት እኛም ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ የሚገባን ወቅት ላይ ነን እላለሁ፡፡ ህገ-መንግስቱና የአዲስ አበባ ህዝብ መብት አንድ ህገ-መንግስት በአንድ መንግስት የተለያዩ መዋቅሮች መካከል ከስልጣን ክፍፍልና ቁጥጥር አኳያ የተለያዩ ወይም ተበላላጭ መብትና ስልጣን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን በአንድ አገር ውስጥ በሚገኙ ዜጎችና ማህበረሰቦች መካከል ተበላላጭ የፖለቲካ መብት እንዲኖር ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ በኛ ህገ-መንግስት ይዘት ላይ በግልጽ እንደሚታዬው ግን የአዲስ አበባ ህዝብ የፖለቲካ መብት ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ጋር ሲነፃፀር በብዙ መጠን ያነሰና የተገደበ ነው፡፡ ይህም በዋናነት ሊሆን የቻለው በሌሎች ክልሎች ለሚኖረው ህዝብ የተሰጡ በርካታ መብቶች በሚሊዬን የሚቆጠር ህዝብ ለሚኖርባት አዲስ አበባ ሳይሰጥ በመቅረቱ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የአዲስ አበባ ህዝብ በህገ-መንግስቱ መሰረት የሚከተሉትን መብቶች አጥቷል፡፡ 2.1. የክልልነት መብት ማጣት አዲስ አበባ የስልጣን ደረጃዋ “ክልል” ሳይሆን አስተዳደር ነው፡፡ ሐረሪንና ቤኒሻንጉል ጉምዝን የመሳሰሉ ከአዲስ አበባ በብዙ ርቀት ያነሰ የህዝብ ቁጥር ያላቸው አካባቢዎች የክልልነት ደረጃ ሲሰጣቸው በሚሊዬን የሚቆጠር ህዝብ ያላት አዲስ አበባ ግን የክልልነት ደረጃ አልተሰጣትም፡፡ ይህም በመሆኑ በውስጧ የሚኖረው ህዝብ ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ተለይቶ የሚከተሉትን መሰረታዊ መብቶች እንዲያጣ ተደርጓል፡ 2.1.1. የፌዴራል መንግስቱ አካል አለመሆን አዲስ አበባና ድሬዳዋ የክልልነት ደረጃ ስላልተሰጣቸው ህገ-መንግስቱ በፌዴራሉ መንግስት አካልነት አያውቃቸውም፡፡ ምክንያቱም በሕገ-መንግሰቱ አንቀጽ 47 መሰረት “የፌዴራል መንግስቱ አካል” ተብለው እውቅና የተሰጣቸው ዘጠኙ ክልሎች ብቻ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግስት አካል ባለመሆኗ ከተማዋም ሆነች በውስጧ የሚኖረው ህዝብ ከሌሎች ክልሎችና ህዝቦች ተለይቶ የሚከተሉትን መብቶች አጥቷል፡፡ ሀ. ወደፊት ክልል የመሆን መብት ማጣት አዲስ አበባ አሁን ላይ የክልልነት ደረጃ አለማግኘቷ አላንስ ብሎ ወደፊትም ክልል የመሆን ዕድል እንዳይኖራት መብቷ ተገድቧል፡ ፡ ምክንያቱም በህገ- መንግስቱ አንቀጽ 47 ቁጥር 2 መሰረት ወደፊት ክልል የመሆን ጥያቄ የማቅረብ መብት ያላቸው በዘጠኙ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ብሔር-ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብቻ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ በዘጠኙ ክልሎች ውስጥ የማይገኝ በመሆኑ ምክንያት የክልልነት ደረጃ የመጠየቅና የማግኘት መብት ህገ-መንግስቱ አልሰጠውም፡፡ ለምሳሌ በክልሎች ውስጥ የሚገኙ በቁጥር አናሳ የሆኑ ሙርሲንና አርጎባን የመሰሉ ህዝቦች ከፈለጉ ክልል የመሆን (ከፈለጉ የመገንጠልም ጭምር) ጥያቄ የማቅረብና ክልል የመሆን መብት ህገ-መንግስቱ የሰጣቸው ሲሆን በሚሊዬን የሚቆጠረው የአዲስ አበባ ህዝብ ግን የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብነትን መስፈርት አያሟላም ተብሎ ስለታመነ ያለአግባብ የክልልነት ጥያቄ የማቅረብ መብት ተነፍጎታል፡፡ ለ. በፌዴሬሺኑ ምክር ቤት አለመወከል በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 61 ቁጥር 1 መሰረት የአዲስ አበባ ህዝብ በፌዴሬሺኑ ምክር ቤት ውስጥ ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ተለይቶ ውክልና ተነፍጎታል፡፡ ማለትም አንድ ወረዳ ወይም ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ቢያቀርብ፣ ወይም አንድ ክልል ከአገሪቱ የመገንጠል ጥያቄ ቢያቀርብ፣ ወይም የፌዴራል መንግስቱ አንድ ቀን ላይ ድንገት ብድግ ብሎ አገሪቱን ለማፍረስ ቢወስን ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ተለይቶ የአዲስ አበባ ህዝብ የእነዚህ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ተጋሪ የመሆን መብት የለውም፡፡ በጥቂት ሺዎች ብቻ የሚቆጠር የህዝብ ብዛት ያላቸው ብሔር-ብሔረሰቦች በሙሉ በፌዴሬሺኑ ምክር ቤት ውስጥ ውክልና ያላቸው ሲሆን ከስድስት ሚሊዬን በላይ እንደሚሆን የሚገመተው የአዲስ አበባ ህዝብ ግንበፌዴሬሺንምክር ቤት ውክልና እንዳይኖረውና ህገ-መንግስቱን የመተርጎም መብት ተጋሪ እንዳይሆን ተደርጓል፡፡ ሐ. የሉዓላዊነትና የአገር ባለቤትነት መብት አለመኖር በወቅቱ የአገሪቱ ህገ-መንግስት መሰረት ሉዓላዊነት ያላቸው ዜጎችና አገሪቱ ሳይሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚባሉ ማንነቶችና ቡድኖች ብቻ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት እነዚህ ቡድኖች የፈጠሯቸው ዘጠኙ ክልሎች (አሁን ላይ 11 ሁነዋል) ያለምንም የፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ ገብነት የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ሉዓላዊ ስልጣን አላቸው፡፡ እነዚህ ክልሎች አገሪቱን በስምምነት ያቋቋሙና የአገሪቱ ባለቤት ስለመሆናቸውም በህገ-መንግስቱ ውስጥ የተደነገገላቸው በመሆኑ ከስልጣን እርከን አኳያ የፌዴራል መንግስቱ የበላይ አለቆችና ባለቤቶች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ግን የአገር ባለቤትነትና ሉዓላዊነት መብት ተጋሪ ስላልሆነች ከሌሎች ክልሎች በተለዬ ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግስቱ እንዲሆንና የአገሪቱ ሉዓላዊነትና ባለቤትነት ተጋሪ እንዳትሆን ተደርጓል፡ መ. የልዩ ጥቅም አለመከበር ህገ-መንግስቱ በአንቀጽ 49 ቁጥር 5 መሰረት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኝ ክልል መሆኑን በመጥቀስ ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም፣ ከመሰረተልማት መስፋፋትና ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ከተማ ላይ እንዲኖረው ደንግጓል፡፡ ያለአግባብ አከራካሪ ሲሆን ቢታይም በእኔ አመለካከት ግን ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ዙሪያ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ጥቅም እንዲኖረው መደረጉ የሚጠበቅና የሚገባ ነው፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ሁኔታ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ተከባ ወይም መሃል ላይ የምትገኝ ከተማ በመሆኗ በኦሮሚያ ክልል ሊኖራት ስለሚገባው ልዩ ጥቅም ህገ- መንግስቱ የደነገገው ነገር የለም፡፡ አንዳንድ የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኞች “የአዲስ አበባን የመጠጥ ውሃ መስመር እንቆርጣለን” በማለት ህዝብን ሲያስፈራሩ፣ “ቆሻሻችሁን ልትጥሉብን አትችሉም” በማለት በህዝብ ላይ ሲዝቱ የሚታየው ህገ-መንግስቱ የአዲስ አበባንና የኗሪዎቿን ልዩ ጥቅሞች የሚያስከብር ግልጽ ድንጋጌ ስለሌለው ነው፡፡ እነዚህ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩ ጉዳዮች አዲስ አበባና ኑዋሪዎቿ በህገ-መንግስቱ መሰረት ያጧቸው መብቶች ሲሆኑ ከዚህም በተጨማሪ ከህግ ውጭ በሆነ መንገድ አዲስ አበባ በርካታ ጥቅሞች እያጣችና መብቷ እየተገፈፈ ይገኛል፡፡ የሚከተሉትን አራት ጉዳዮች በምሳሌነት ማዬት ይቻላል። #አንደኛ፡- አዲስ አበባ በአገሪቱ ህገ-መንግስት ድንጋጌ መሰረት የምትጠራበት ስም “አዲስ አበባ” ሆኖ እያለ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ልሂቃን የሚጠሯት ግን “ፊንፊኔ” ብለው ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተቆረቆረችበት ዕለት ጀምሮ ይዛው የኖረችውን ስም ያለአግባብ ቀይሮ በአንድ ትንሽ መንደር ወይም አካባቢ ስም “ፊንፊኔ” ተብላ እንድትጠራ መደረጉ ህገ ወጥነት ነው፡፡ #ሁለተኛ፡- የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ ማስተዳድር እንዳለበት በህግ ተደንግጎ እያለ ይህ መብቱ ግን በተደጋጋሚ ሲጣስ ታይቷል፡፡ ከአቶ ተፈራ ዋልዋ ጀምሮ አስከ የአሁኗ ወ/ሮ አዳነች አበቤ ድረስ ለአዲስ አበባ የተሾሙላት ከንቲባዎች በሙሉ ከክልል የመጡና እንኳንስ የከተማ አስተዳደርን የከተማ ኑሮንም በቅጡ የማያውቁ ናቸው፡፡ ካላቸው ልዩ ባህሪ አኳያ ከተሞች በከተማ አስተዳደር ጉዳይ ላይ በቂ ልምድና ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎች መተዳደር ሲገባቸው አዲስ አበባ ግን ለአለፉት 32 ዓመታት የተመራችው አዲስ አበባን ሲያዩኒውዮርክንና ፓሪስን እንዳዩ በደስታ በሚደመሙ የገጠር ካድሬዎች ነው፡፡ አንዳንዴም የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ያልሆኑ ሰዎች ለአዲስ አበባ ከተማ ከህግ ውጭ ከንቲባ ሆነው ሲሾምላት ታይቷል፡፡ ባልተጻፈ ህግ መሰረትም ለአለፉት 18 ተከታታይ ዓመታት በቋሚነት የአዲስ አበባ ከንቲባዎች ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ብቻ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ #ሦስተኛ፡- የኦሮሚያ ክልል ያለምንም ህጋዊ መሰረት ከሌሎች ክልሎች ተለይቶ የክልሉን ዋና ከተማ አዲስ አበባን አድርጓል፡፡ አንድ ክልል የራሱ ክልል አካል ያልሆነን ሌላ ከተማ ዋና ከተማ አድርጎ መጠቀሙ በየትም ዓለም ያልተለመደና በኛም አገር ምንም ዓይነት ህጋዊ ድጋፍ የሌለው ውሳኔ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም የአዲስ አበባ ህዝብ ልጆቹ ያለፍላጎታቸው የኦሮሚያን ክልላዊ መዝሙር እንዲዘመሩ፣ የኦሮሚያን ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቅሉና ያለፍላጎታቸው በኦሮምኛ ቋንቋ እንዲማሩ ሲገደዱ አይተናል፡፡ የኦሮሚያ ፖሊሶችም ያለ ክልላቸው በአዲስ አበባ ፀጥታ የማስከበር ህገ-ወጥ ኃላፊነት እንዲኖራቸውም ሲደረግ ታይቷል፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ግን ያለምንም ህጋዊ መሰረት ነው፡፡ #አራተኛ፡- ከሁሉም በላይ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” በሚል እየቀረበ ያለው ጥያቄ ቀስ በቀስ እንድንለማመደው እየተደረገ ያለና የከተማዋንም ሆነ የአገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ጥያቄ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ አዲስ አበባ ተጠሪነቷ ለፌዴራሉ መንግስት መሆኑንና የፌዴራሉ ርዕሰ ከተማ መሆኗን በግልጽ መደንገጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ልዩ ጥቅም እንዲኖረው በግልጽ መደንገጉ በራሱ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አለመሆኗን በማያሻማ ሁኔታ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ባለቤት ቢሆን ኖሮ “ሙሉ ጥቅም” እንጅ “ልዩ ጥቅም” እንዲኖረው አያስፈልግም ነበር፡፡ በአጠቃላይ የኦሮሞ ብሔርተኞች “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” ለሚለው አቋማቸው በመከራከሪያነት ሊያቀርቡ የሚሞክሩትም ተገቢ የሆነ ህጋዊ ድንጋጌን ሳይሆን “አዲስ አበባ ጥንት የኦሮሞዎች መኖሪያ ነበረች” የሚል ከባለቤትነት መብት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው፣ አገሩ የተካለለው በታሪክ ሳይሆን በማንነትና በቋንቋ መስፈርት መሆኑን የረሳ ውሃ የማይቋጥር መከራከሪያ ነው፡፡ የሚገርመው ይህ ሁሉ ህገ-ወጥ ጥያቄ በአዲስ አበባ ላይ ሲቀርብ በስልጣን ላይም ሆነ በተቃዋሚነት ከሚገኙት የኦሮሞ ተዋቂ የፖለቲካ ሰዎች መካከል አንዳቸውም የህግና የመርህ ተገዥ በመሆን ለመቃዎም ሲሞክሩ ታይቶ አያውቅም፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ለምንድን ነው? ይህንን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ህገ-መንግስቱን ባረቀቁና ባጸደቁ የፖለቲካ ኃይሎች በኩል የነበረውን ፍላጎት አሁን ላይ ካለው የኦሮሞ ብሔርተኞች ፍላጎትና ዓላማ ለይቶ ማዬት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ 1983 ዓ ም ላይ ወደ ስልጣን የመጡትና የህገ-መንግስቱ አርቃቂዎችና አጽዳቂዎች የነበሩት የፖለቲካ ኃይሎች መሰረታዊ ፍላጎት አገሪቱን ከነሱ የፖለቲካ አደረጃጀት ጋር በሚያጣጥም ሁኔታ በቋንቋና በብሔር ማንነት መስፈርት ከፋፍሎ ማደራጀት ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ህገ-መንግስቱን ያረቀቁት የፖለቲካ ኃይሎች ህገ-መንግስቱን ያወጡት የአንድ አገር አካል ሆነው አስከወዲያኛው ለመኖር በመወሰን ሳይሆን ሲቻልየበላይነትን አስጠብቆ አብሮ ለመኖር፣ ሳይቻል ግን ተገንጥለው በመውጣት የራስን አገር የማቋቋም መንታ ፍላጎት ይዘው ስለነበር ነው፡፡ በአጭሩ እነዚህ ኃይሎች ህገ-መንግስቱን ያረቀቁት አገሪቱን አንድነቷ ምልዑ ሆኖ እንደሚቀጥል ቋሚ አገራቸው በማዬት ሳይሆን እንደ ጊዜያዊ የኪራይ ቤት በመቁጠር ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከተፈጥሯዊ ማንነቷ ጋር በተያያዘ አንድ የብሔር ባለቤት ሊኖራት የማይችለውና ቅይጥማንነት ያላት አዲስ አበባ የክልልነት መብት እንዳይኖራት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በህገ-መንግስቱ አርቃቂዎች ዘንድ “አዲስ አበባ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ውድቀት የተገነባች፣ የነፍጠኛና የትምክህተኞች ምሽግ ነች” የሚል አቋም ስለ ነበራቸው መብቷን የመገደብ ፍላጎታቸው ከዚህ የተዛባ አስተሳሰባቸው የመነጨ ነበር፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የወቅቱ የኦሮሞ ብሔርተኛ ኃይሎች ግን አዲስ አበባን በሚመለከት እያራመዱት ያለው አቋም ከቀድሞዎቹ የህገ-መንግስት አርቃቂዎች ጋር የሚገናኝበት የራሱ አንጓ ቢኖረውም ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት ነው ማለት ግን አይቻልም ፡፡ የወቅቱ የኦሮሞ ብሔርተኞች የአዲስ አበባ ከተማ ብቸኛ ባለቤት የመሆን ፍላጎት ጎልቶ እየመጣ ያለው “አገረ-ኦሮሚያን” ለመመስረት ተቃርበናል፣ ይህንን ዓላማ በብቃት ለማሳካትም አዲስ አበባን አስቀድሞ አለመቆጣጠር እንቅፋት ይሆንብናል፣ እንቅፋት ከመሆንም በላይ የመጨረሻ ነፃ አገር የመመስረት ስኬታችንን ጎደሎ ያደርገዋል የሚል ስጋት ስለአደረባቸው ነው፡፡ አዲስ አበባ ከሌላ ከማንኛውም ክልል ጋር ሳትዋሰን ሙሉ በሙሉ በኦሮሚያ ክልል ተከባ የምትገኝ ስለሆነች እሷ የኦሮሚያ ክልል አካል ባልሆነችበት ሁኔታ “ኦሮሚያ” የሚባል ወጥ የሆነ አገር መፍጠር አይቻልም፡፡ አዲስ አበባ በኦሮሚያ አካልነት ካልተካተተች እንደ ሳንማሪኖ /Sanmarino/ ወይም ሌሴቶ/Lesotho/ በአንድ አገር ውስጥ ተከባየምትገኝ ሌላ“ደሴት አገር” ትሆናለች ማለት ነው፡፡ ይህ እውነታ ነው የአምልኮ ያህል እናምንበታለን የሚሉትን ህገ-መንግስት በመቃረን ጭምር አዲስ አበባ የሁላችን ነች ሳይሆን በተለየ ሁኔታ “የኦሮሞ ናት” እንዲሉ ያስገደዳቸው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች ከመቸውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቀት ከፍተኛ የታጠቀ ኃይል አለን፣ በፌዴራሉ መንግስትም የበላይነት ይዘናል፣ ሊቀናቀነን የሚችለው “የአቢሲኒያ” ኃይልም እርስ በርሱ እየተዋጋ ተዳክሟል ብለው ስለአሰቡ “አገረ-ኦሮሚያን” ለመመስረት ከመቸውም ጊዜ በላይ የተመቸው ጊዜ ዛሬ ነው የሚል እምነት ያሳደሩ ይመስላሉ፡፡ በአጠቃላይ በህገ-መንግስቱ የቀድሞ አርቃቂዎችና አጽዳቂዎች ዘንድ አዲስ አበባ የጥቃት ዒላማ የሆነችው እንደማንኛውም የአገሪቱ ከተሞች ከብሔር አደረጃጀት ጋር የማትጣጣምና የኢትዮጵያዊነት የፖለቲካ አመለካከት ምሽግ ተደርጋ የምትታይ በመሆኑ ነው፡፡ በአሁኖቹ የኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ የጥቃት ዒላማ የሆነችው ደግሞ ለሚመኙት የአዲስ አገር ምስረታ ፊታቸው ላይ ቆማ እንቅፋት ስለሆነችና የመጨረሻ የድል ሪቫናቸውን ሊቆርጡባት የወሰኑ የመጨረሻ ቋጠሮ በመሆኗ ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞችና የመገንጠል ጥያቄ በአዲስ አበባ ዙሪያ የገጠመን ችግር መፍትሄው ቀላልም ከባድም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድ አገር ህዝብነትና በእኩልነት አብረን ለመቀጠል ከወሰን መፍትሄው በእርግጥም ቀላል ነው፡፡ መነጣጠልን ግባችን አድርገን ከወሰድን ግን የአዲስ አበባ ጉዳይ ጭራሹንም መፍትሄ የለሽ ነው፡፡ የብሔርተኝነት ፖለቲካ አንድ ጊዜ የሆነ የጥንካሬ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ “ነፃ አገር” ከመመስረት ያነሰ ማንኛውም ዓይነት ውጤት ሊያረካው አይችልም፡፡ ብሔርተኝነት እደርስበታለሁ የሚለው የመጨረሻ ውጤት ላይ ደርሶ እስከ መጨረሻው ከቅራኔ አዙሪት እንደማይዎጣ ካላዎቀ ወይም ራሱን በልቶ ካልጨረሰ በስተቀር ነጭናጫና አልቃሻ ከመሆን ሊላቀቅ አይችልም፡፡ የወቅቱ የኦሮሞ ብሔርተኞች ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዬንም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች በቅድሚያ ትልቅ ክልል መፍጠርና አንፃራዊ የሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር ዕድል አገኙ፣ ከዚያም ጥያቄያችን አልተመለሰም ብለው በመታገልም በፌዴራሉ መንግስት የመሪነት ድርሻ አገኙ፣ ይህም ሁሉ ሆኖ ግንአሁንም ከሌላው ህዝብ በበለጠ እኛ ተበዳይ ነን ብለው ሲጮሁና ከዚያም አልፈው የመገንጠል ዓላማን ለማሳካት ሲጥሩ እያዬን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ እየታዬ ያለው የወቅቱ ችግርም እኩል ወይም የበላይ ከመሆንም ባለፈ ትልቅ አገርን አፍርሶና የህዝብን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎ የራስን ነፃ አገር የመመስረት ፕሮጀክት አካል ነው፡፡ ምክንያቱ ይህ ባይሆን ኖሮ አዲስ አበባ የእኛ ብቻ ነች ለማለት የሚያስደፍር ምንም ዓይነት አመክንዮ ሊኖር አይችልም፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች “ነፃ አገር” የመመስረት ጥያቄ ለእነሱ በርግጥም አንድ “ነፃ አገር” የመመስረት ፍላጎት ነው፡፡ ጥያቄው የህዝብ ነው ወይንስ የጥቂቶች? የሚል ጥያቄ መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ከመብት አንፃር እንዲህ ዓይነት ጥያቄ መነሳቱ እንደ አንድ የፖለቲካ ጥያቄ ቢታይ ችግር የለውም፡፡ ለጥያቄው ተገቢ መፍትሄ ለመስጠት መሞከርም አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የወቅቱን የኦሮሞ ብሔርተኞች የመገንጠል አጀንዳ ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት አኳያ ልናየው ስንሞክር ግን አጀንዳው የኢትዮጵያ ህልውና የመቀጠልና ያለመቀጠል ጥያቄ ሆኖ እናገኘዋልን፡፡ ማለትም “ኦሮሚያ” ክልል አሁን ላይ ያለውን የግዛት መጠን እና ቅርፅ ይዞ ወደ አገርነት ቢቀየር አዲስ አበባና ሐረሪ ክልል ከመላው የአገሪቱ ክፍል የሚነጠሉ ከመሆኑም በላይ የአገሪቱ የሰሜን እና የደቡብ ክፍልም በየብስም ሆነ በባህር በማይገናኙበት ሁኔታ ይለያያሉ፡፡ በጠባብ የመሬት ኮሪደር ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጋር የሚገናኘው የምስራቁ የአገራችን ክፍልም ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ አካል ሆኖ የሚቀጥልበት ዕድልም የጠበበ ነው፡፡ እንዲያውም የኦሮሞ ብሔርተኞች በሶማሌላንድ በኩል የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው እየሰማን ስለሆነ የአገራችን የሰሜኑና የምስራቁ ክፍል የመለያየቱ እድልም ሰፊ ነው፡፡ በዋናነት ግን ኦሮሚያ ክልል በሁለቱ የሰሜንና የደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች መሃል ላይ የሚገኝ በመሆኑ እሱ ከመሃል ተነጥሎ አገር ሲሆን (በዚህ ጽሁፍ የሽፋን ሥዕል ላይ እንደሚታየው) ከዚያ በኋላ አንድ ሁኖ የሚቀጥል “ኢትዮጵያ” የሚባል አገርም ሆነ “የኢትዮጵያ” የሚባል መንግስት አይኖርም፡፡ የዚህንጉዳይ ክብደት ራሴን ምሳሌ አድርጌ ለመግለጽ ልሞክር፡፡ በእኔ በኩል የኦሮሞህዝብ ለመብቱመከበር አስካሁን ያደረገውን ትግል እደግፋለሁ፡፡ ወደፊትም ለዴሞክራሲና ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያደርገው ትግል ተገቢና የሚደገፍ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያም አልፎ በአንድ አገር የመገንጠል ጥያቄ ጭምር እውነተኛ የህዝብ ጥያቄ ሆኖ ገፍቶ ከመጣም ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ሊስተናገድ ይገባል የሚል እምነት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ይሁንና የኦሮሚያን የመገንጠል ጥያቄ ግን በአንድ አሳማኝ ምክንያት ልቀበለው አልችልም፡፡ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ኦሮሚያ ሲገነጠል ኢትዮጵያ በርግጠኝነት ስለምትፈርስ የቱንም ያህል ለሌሎች መብት ተቆርቋሪ ሰው ብሆንም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አገርና ዜግነትን የሚያሳጣኝን ጥያቄ በፀጋ ልቀበል አልችልም፡፡ ልቀበል የማልችለውም የኦሮሞ ተወላጅ ስላልሆንኩ ሳይሆን አገርና ዜግነቴን ማጣት የማልፈልግና የማይገባኝ ሰው በመሆኔ ነው፡፡ ማንም ከኦሮሞ ብሔርተኞችና ከጽንፈኛ ደጋፊዎቻቸው በስተቀር ሌላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ከእኔ የተለዬ አቋም ይኖረዋል ብዬም አልገምትም፡፡ ዜጎች ብቻ ሳንሆን የመገንጠሉ ጥያቄ በሚቀርብበት ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስትም ጥያቄውን ሊቀበል የሚችልበት አሳማኝ ምክንያት አይኖርም፡ ኦሮሚያ ከተገነጠለች በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ሆኖ ሊቀጥል የሚችል አካል ስለማይኖር በስልጣን ላይያለው መንግስት አምባገነናዊም ይሁን ዴሞክራት፣ አንቀጽ 39ን የሚደግፍም ይሁን የሚቃዎም የራሱን ህልውና የሚያሳጣውን የኦሮሚያ የመገንጠል ጥያቄ በፀጋ ሊቀበለው አይችልም፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች በሆነ ተዓምር አዲስ አበባና ሐረሪን ጨምሮ ቀሪው የአገሪቱ ክፍል ከኦሮሚያ መገንጠል በኋላ አንድ ሆኖእንዲቀጥል የሚያስችል ዋስትና ካልሰጡ በስተቀር የአገሪቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ራሱንም ሆነአገሪቱን የሚያፈርስ የህዝበ-ውሳኔ ጥያቄ ሊቀበል አይችልም። ህጋዊነት ባለው ህዝበ-ውሳኔ ያልተረጋገጠና በፌዴራል መንግስቱ እውቅና ያልተሰጠው የመገንጠል ጥያቄ ደግሞ አለም አቀፍ እውቅና በማጣት እየዋተተች ከምትኖረው ከሶማሌላንድ ጋር ሊቀራረብ የሚችል አገራዊ ህልውና ሊያስገኝ እንኳ አይችልም። ከዚህ የምንረዳው የኦሮሚያ የመገንጠል ጥያቄ በሠላማዊና ህጋዊ መንገድ እውን ሊሆን የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ጥያቄውን በኃይል ለማስፈጸም መሞከር ደግሞ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ አገርና ዜግነትን የሚያሳጣው የኦሮሚያ የመገንጠል ጥያቄ አፍጥጦ ሲመጣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አነስተኛ ጥቅሞችና ጊዜያዊ ስሜቶች ተበታትኖ የሚታየው የፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ በከፍተኛ ፍጥነት መለዎጡ አይቀሬ ነው፡፡ በቅርቡ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መነካት ምክንያት ከታየው በብዙ እጥፍ የበለጠ የህዝብ ቁጣ እንደሚፈጠር ጥርጥር የለውም። እንኳንስ በህዝቡ ውስጥ በገዥው ፓርቲና በማዕከላዊ መንግስት ውስጥ ያለው የኃይል ሚዛንም እንዳልነበረ ሆኖ ይፋለሳል፡፡ አብዛኛው የአገሪቱ ህዝብ ከኦሮሞ ብሔርተኛው በተፃራሪ በጋራ በመቆም ህልውናውን ለማስከበር መታገሉ አይቀሬ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተያይዞ የመጥፋት አደጋ አፍጥጦ ሲመጣም ራሳቸው የኦሮሞ ኃይሎችም ከመከፋፈል አደጋ ይተርፋሉ ብሎ ማሰብ ስህተት ይሆናል፡፡ ሚሊዬኖች በከንቱ እንዲያልቁ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር በዚህ አይነቱ የኃይል አሰላለፍ ትግልም የኦሮሞ ብሔርተኞች አሸናፊ ሆነው የሚወጡበት ዕድል አይኖርም፡፡ ወይ ይሸነፋሉ፣ ወይም ሁላችንም መሸናነፍ ተስኖን አገሪቱ ወደ ለዬለት የመፈራረስ አደጋ ትገባለች፡፡ እንደ ዶሮዋ “ባልበላውም ጭሬ ልበትነው” ለማለት ካልሆነ በስተቀር ከመገንጠል ጥያቄ የኦሮሞ ህዝብ ተለይቶ ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ የዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ ከኦሮሞ ብሔርተኞች ጋር የተያያዘ ስለ ሆነ ነው እንጂ የሁሉም የአገራችን ብሔርተኞች ሚና ከዶሮዋ አባባል የተለዬና የተሻለ አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው በሃያ ሰባት ዓመቱ የኢህአዴግ ዘመን እንደ ህወሃት የፀጥታ ተቋማትን በበላይነት የተቆጣጠረ፣ የአገሪቱን ብሔር-ብሔረሰቦች ድጋፍና አጋርነት አግኝቻለሁ ብሎ የሚያምን፣ በአካባቢው ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ድጋፍ ያገኘ፣ በፈለኩት ጊዜ በአንቀጽ 39 አማካኝነት በቀላሉ ነፃ አገር የመፍጠር መብትና ዕድል አለኝ ብሎ የሚመካ የፖለቲካ ኃይል አልነበረም፡፡በመጨረሻ ግን ራሱንም ሆነ የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ የህልውና አደጋ ያጋለጠ ከበባ ውስጥ አገኘው እንጂ አለኝ የሚለውን ጉልበትና ድጋፍ ሁሉ ከአጠገቡ አላገኘውም፡፡ የኢትዮጵያ መፍረስ በቀጠናው ሠላምና ደህንነት ላይ የሚያስከትለው ቀውስ ቀላል ስለማይሆንም የኦሮሚያ የመገንጠል ጥያቄ በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድም ተቀባይነት እንደማይኖረው ከወዲሁ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ህወሃት ባለፈው ዓመት ጦርነት ጣርማ-በር ከደረሰ በኋላ የአገሪቱ ህልውና ጉዳይአሳሳቢ ሆኖ ሲታይ ከምዕራባዊያኑ የገጠመው ፈተና ምንያህል ከባድ እንደነበር አይተናል፡፡ በፕሪቶሪያው ስምምነት ህወሃት የአገሪቱን የግዛት አንድነት ጥያቄ ውስጥ ላለማስገባት ለምን ለመስማማት እንደተገደደም ቆም ብሎ ማሰብና ከዚህ የቅርብ ጊዜ ሂደት ተገቢ ትምህርት መውሰድ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ስለሆነም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በስልጣን ላይ የሚገኘው ማዕከላዊ መንግስትና ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ሊደግፈው የማይችልን አገር የሚያፈርስ የመገንጠል ጥያቄ በእልህ ይዞ መቀጠል የኦሮሞ ህዝብ በእስካሁኑ ትግል ያገኛቸውን ውጤቶች ሁሉ ከንቱ የሚያስቀር እንጂ ለተሻለ ውጤት የሚያበቃው አይሆንም፡፡ ጭቆናንና ድህነትን በመገንጠል ሸሺቶ ማምለጥ እንደማይቻልም ከኤርትራና ከደቡብ ሱዳን ለመማር መሞከር ይጠቅማል፡፡ በአገራችን ታሪክ እንኳንስ በአንድ ሰላማዊ የትግል ሂደት ተመርጬ ለስልጣን በቅቻለሁ የሚል ሀይል ይቅርና ከአንድ የአካባቢ ሽፍትነት ተነስተው ለአገር መሪነት የበቁ ንጉሶችም መጨረሻ ላይ ውድ ህይወታቸውን ጭምር አሳልፈው ሲሰጡ የታየው ለአገር አንድነትና ህልውና ነው። የወቅቱ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከዚህ በጎ የታሪክ ሂደት በተቃራኒ ሲጓዙ መታየታቸው ግን የአመራር ብቃታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባና ለታላቁ የኦሮሞ ህዝብ የማይመጥን አካሄድ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ለማናችንም የማይበጅ አውዳሚ ጥያቄ ከሌላው ህዝብ ባልተለዬ ሠላም ወዳዱ የኦሮሞ ህዝብ ሊቃወመውና ሊታገለው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ከፈረሰች በኋላ ከፍርስራሹ ተርፎና ሠላም አግኝቶ የሚቀጥል ትንሽም ይሁን ትልቅ አገር የለም፡ ኢትዮጵያ ከፈረሰች የእኛ እጣፈንታ ከድህረ ሲአድባሬ ሶማሊያ ወደባሰ ሁኔታ እንጂ ወደ ድህረ ሶቬት ህብረትና ዩጎዝላቪያ ሁኔታም የመሸጋገር ዕድል አይኖረውም፡፡ እንደ አንድ ወጥ “አገረ ብሔር (Nation state)” የምትታዬው ሶማሊያ ገብታ ልትዎጣበት ያልቻለችውን ችግር በዘር መጠፋፋት (Genocidal) የእርስ በእርስ ጦርነት እየተፋጀን የምንገኘው ኢትዮጵያውያን በቀላሉ ገብተን ልንዎጣበት አንችልም፡፡ አገሪቱን ከመፍረስ ለመታደግ የሚያስችል አቅምም ሆነ ፍላጎት ያጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም የሲአድባሬ፣ ወይም የጋዳፊ ፣ ወይም የሜሎሶቪች ዕጣ-ፈንታ እንጂ የሚካኤል ጎርቫቾቭ ዕድል ሊኖራቸው አይችልም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ገና ያልተፈቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች አሁንም ያሉት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ ላይ ግን ከሌላው ህዝብ በተለዬ ተበዳይና አልቃሽ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የኦሮሞን የእኩልነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞን የአገር መሪነት ጭምር በፀጋ የሚቀበል ስለመሆኑ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ በነቂስ ወጥቶ በመደገፍ በተግባር አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መታማት ካለበት ዶ/ር ዐቢይን ያለምክንያት በመደገፉ ነው እንጂ ያለ ምክንያት በመቃዎም አይደለም፡፡ እነዚህን አዎንታዊ ለውጦች ግምት ውስጥ በማስገባት የኦሮሞ ብሔርተኝነት ሊሰክን ይገባል፡፡ በተለይም የኦሮሞ ልሂቃን ክልላቸውን ሙሉ ለሙሉ በብቸኝነት ከማስተዳደር አልፈው በአዲስ አበባና በማዕከላዊ መንግስቱ የበላይነቱን በያዙበት በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ብሔርተኞች አገርን የሚያፈርስ የተገንጣይነት አጀንዳ ይዘው መቀጠላቸው የሚያሳዬን ምን ያህል ስሜታዊና እንወክለዋለን ለሚሉት ለኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም የማይጨነቁ መሆናቸውን ነው፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን ትግል በሂደት በአገር ደረጃ ገንቢ ሚና ለመጫዎት ወደሚያስችል (በተወሰነ ደረጃ ወዳጀ ጃዋር መሃመድ አሁን ላይ እያሳየው ወዳለው ዓይነት) ስክነትና ምክንያታዊነት መሸጋገርና ማደግ ሲገባው ወደ ባሰ ጽንፈኝነትናተገንጣይነት አቋም ሲሸጋገር ማዬታችን እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የሚገርመው የአገሪቱን መሪ ጨምሮ አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን የኦሮሞን ህዝብ ለባሰ ሰቆቃ የዳረገውን የወቅቱን የዶ/ር ዐቢይንና የክሊኮቻቸውን ስርዓት “የኦሮሞ ስርዓት” አስመስለው ሆን ብለው ለመናገር ሲደፍሩ እያየን ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ በአገር ደረጃ የመንግስት ስልጣን ላይ ያለ ኃይል በሌሎች ውጫዊ ኃይሎች ሊታማ ወይም ሊፈረጅ ይችላል እንጂ ራሱን በተለየ ሁኔታ የአንድ ብሔር መንግስት አድርጎ ሲገልጽ መስማት በፍጹም ያልተለመደ ነው። እስካሁን እራሱን በብሔር ነፃ- አውጭነት ስም የሚጠራው ህወሃት እንኳን የ27 ዓመቱን ስርዓት የትግራይ ስርዓት አድርጎ በመግልፅ ሲሳሳት ሰምተነው አናውቅም፡፡ እንኳንስ ህዝቡ ያለአግባብ መፈረጁን በኢህአዴግ ውስጥ ህወሃት የበላይ የመሆኑን ሃቅም አምነው ተቀብለው አያውቁም፡፡ እንዲህ አይነቱን የተሳሳተ አቋም የወቅቱ የኦሮሞ ልሂቃን በገሃድ ሲያራምዱ ማየት ምን ያህል ለኦሮሞ ህዝብ ደህንነት የማይጨነቁና የሚሰሩትንም በአግባቡ የማይረዱ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። የንጉሱና የደርግ ስርዓት በአማራ ስርዓትነት፣ የ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ ስርዓት በትግራይ ስርዓትነት በመፈረጁ የአማራ ህዝብና የትግራይ ህዝብ ያለአበሳቸው በየተራ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ተደጋጋሚ ስህተት መማር ተስኖን የኦሮሞን ህዝብ ለተመሳሳይ ጥቃት ልንዳርገው አይገባም፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች ጥያቄ ምን ያህል ወደባሰ የእብደት ደረጃ እያደገ እንደሆነ ስለግልፅነታቸው ምስጋና ይግባቸውና ኮሎኔል ገመቹ አያና ሰሞኑን በሰጡት ቃለ መጠየቅ በግልፅ ነግረውናል-፡፡ ኮሎኔሉ “አገረ ኦሮሚያ” በምን ዓይነት ስልትና ዕቅድ እውን እንደምትሆን በሚከተለው ሁኔታ ገልፀውልናል፡፡ ኦሮሚያ ነፃ ስትወጣ አቢሲኒያዎች (አማራዎችና ትግሬዎች ማለት ነው) በቅድመ ሚኒሊክ ዘመን ወደነበሩበት ቅርጻቸው እንደሚመለሱ፣ አማራ የሚባል ህዝብም ሊኖር የሚችለው ደብረ-ብርሃን አካባቢ ብቻ እንደሚሆንና ቀሪው የአማራ ክልል ግን ባለቤቶቹ ሌሎች /ማለትም ቅማንት፣ አገው፣ ኦሮሞ፣ ትግራይ፣ አርጎባ/ እንደሚሆኑ፤ ሐረሪን የመሳሰሉ ራሳቸውን ችለው አገር መሆን የማይችሉ ሌሎች ክልሎችም በአገረ ኦሮሚያ ተካተው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ፣ በኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ በሚሊዬን የሚቆጠሩ አማራዎች፣ ጉራጌዎችና ትግሬዎችም የእኔ የሚሉት መሬት እንደማይኖራቸውና በኦሮሚያ ውስጥ መኖር የሚችሉትም ዜግነታቸው ኦሮሚያ ከሆነና የገዳ ስርዓትን ከተቀበሉ ብቻ እንደሆነ፣ ይህንንም ዓላማ የኦሮሞ ብሔርተኞች በኃይል ከማስፈፀም ወደኋላ እንደማይሉ በእርግጠኝነት አብራርተው ኮሎኔሉ ነግረውናል፡፡ ከዚህ የኮሎኔሉ ንግግር በግልፅ የምንረዳው- እንድትፈጠር የምትታሰበው “አገረ-ኦሮሚያ” ሰዎች ዜግነታቸውንና ባህላቸውን ካልቀየሩ በስተቀር ሊኖሩባት የማይችሉ በዓለም ብቸኛዋና የመጀመሪያዋ አገር የምትሆን መሆኑን ነው፡፡ ይህም በወለጋ እየተካሄደ ያለው ዘርን የማጽዳትና ዘርን የማጥፋት እርምጃ አንድ ወጥ ማንነት ብቻ ያለውና የሌሎችን ማንነት ያጠፋ አሃዳዊ “አገረ-ኦሮሚያን” የመፍጠር ፕሮጀክት አካል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የታገልነው ራሳችንን ከማንነት ጭቆና ነፃ ለማውጣት ነው ሲሉን የነበሩና በፌዴራሊዝም ጠበቃነት ሲመፃደቁ የኖሩ የኦሮሞ ብሔርተኞች ዛሬ ላይ ጡንቻችን ፈርጥሟል ብለው ሲያስቡ እንደዚህ የአሃዳዊነትና የአዋሃጅነት /Assimilation/ ዓላማ አራማጅ ሲሆኑ ማየታችን ከብሔርተኝነት ፖለቲካ የሚጠበቅ በጎ ነገር አለመኖሩን የሚያረጋግጥልን ነው፡፡ በእርግጥም ከእዚህ የኮሎኔሉ ንግግር በላይ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ተባብሮ በጋራ እንዲቆም የሚያደርግና የህይዎት መስዋዕትነት ጭምር እንዲከፍል የሚያስገድድ አሳሳቢ አጀንዳ ያለ አይመስለኝም፡፡ በአጠቃላይ የኦሮሞ ብሔርተኞች አሁን ላይ የያዙትን የተሳሳተ አካሄድ በአስቸኳይ ካላቆሙ ሌላውን ህዝብ ከእነሱ ወደ ባሰ የብሔርተኝነት ስሜት እንደሚገፉት፣ ሌላው ህዝብም ከእነሱ በተፃራሪ በአንድነት ለመቆም እንደሚገደድ፣ በማዕከላዊ መንግስቱ አሁን ላይ ያላቸው የበላይነትም ህወሃት ላይ ሲሆን እንደታየው በአጭር ጊዜ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል፣ የአዲስ አበባን ህዝብ በከበባ እናንበረክከዋለን ብለው ሲያስቡም የራሳቸውን ህዝብ በሌሎች የባሰ ከበባ ውስጥ ሊጥሉት እንደሚችሉ፣ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤትም በእስካሁኑ ትግል የተገኘውን ውጤት ሁሉ ከንቱ ሊያስቀር የሚችል ከባድ ሸንፈት ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ለኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅምና የወደፊት ታሪክ ስለማይጠቅምም የኦሮሞ ብሔርተኞች አካሄዳቸውን ሰከን ብለው መፈተሽና ማስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡ #መፍትሄውስ ወዴት ነው? የመብት መከበር ሁልጊዜም አንጻራዊ እንጂ በማንኛውም ሁኔታ ሊተገበር የሚችል አጉራ ዘለልነት አይደለም፡፡ በአንድ አገርና ህዝብ ህልውና ማጣት ሊከበር የሚችል የማንም የነፃነት ጥያቄ ሊኖር አይችልም። ለህዝብ ደህንነት ኃላፊነት የሚሰማውና ምክንያታዊ የሆነ የፖለቲካ ኃይል “የእኔ ፍላጎት ከተሳካ ስለሌላው ምን ይገደኛል” ሊል አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ስርዓተ-መንግስት እንዲኖረው ያስፈለገው የጋራ ደህንነትን ለማስጠበቅ ተብሎ እንደሆነ ይረዳል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኞች ይህንን እውነታ በመገንዘብ ተያይዞ ከመጥፋት ይልቅ በእኩልነትና በአንድነት አብሮ መኖርን ቢመርጡ ለሁላችንም የተሻለ ይሆናል፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይ ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ በቀላሉ ሊያገኝ የሚችለው የመገንጠል ጥያቄ ተወግዶ አገሩም ሆነ የአገሩ ርዕሰ ከተማ የጋራ መኖሪያችን መሆኑን አምነን ስንቀበል ብቻ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል በታሪክ ሂደት ከኢትዮጵያ ጋር የተጋመደበት ነባራዊ ሁኔታ የአገሩ ዋና ካስማና ማገር ሆኖ እንዲኖር የሚያደርግ ነው እንጂ ተነጥሎ እንደ አገር ለመቆም የሚያስችለው አይደለም፡፡ ይልቁንም በአዲስ አበባ ዙሪያም ሆነ በመላው አገሪቱ የኦሮሞ ህዝብ ያለው አሰፋፈር ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ በተሻለና በተለዬ ተጠቃሚ የሚያደርገው ነው፡፡ ይህንን በጥሩ የታሪክ አጋጣሚ የተገኘ ዕድል ተጠቅሞ መልማትና የልጆቹን የወደፊት ህይወት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ነው እንጂ አገርን የሚበትን አጀንዳ ማራመድ በየትኛውም መመዘኛ ለኦሮሞ ህዝብ አይጠቅመውም፡፡ አይመጥነውምም። በአጭሩ የኦሮሞ ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆነው ከመገንጠል ሳይሆን እኩልነት፣ ዴሞክራሲና ብልጽግና ከሰፈነባትና ጠንካራ አገራዊ አንድነት ካላት ኢትዮጵያ ነው፡፡ ስለሆነም የኦሮሞ ብሔርተኞች ጥያቄ በእርግጠኝነት ሊተገበርና፣ ሲተገበርም ህዝቡን በዘላቂነት ሊጠቅም ወደሚችል ምክንያታዊና ተጨባጭ ጥያቄ ሊለወጥና ሊያድግ ይገባል፡፡ በእኔ አመለካከት የወቅቱ የኦሮሞ ልሂቃን አጀንዳዎች ከፅንፈኛ ብሔርተኝነት ስሜት የተላቀቁና የሚከተሉትን ዓይነት ይዘት ያላቸው ቢሆኑ ተመራጭ ነው እላለሁ፡፡ እነሱም፡- በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የገጠር ቀበሌዎች በስፋት ወደ አዲስ አበባ ይካተቱልን፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከተሟላ መብት ጋር የመሬታቸው ሙሉ ባለቤት ይሁኑ፣ ክልላችን ከአግባብ በላይ የሰፋ ስለሆነ ባልተማከለ ሁኔታ አራት ወይም አምስት ክልል የመሆን መብት ይሰጠን፣ በክልላችን ውስጥ የራሳችን ርዕሰ ከተማና ሌሎች ሰፋፊ ከተሞችን የማቋቋም መብት ይኑረን፣ የኦሮሞ ህዝብ በነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ወኪሎቹን የመምረጥ መብቱ ይከበር፣ በክልላችን ሙስና ተወግዶ ስራ ፈጠራና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የሚያስችል የህዝብና የካፒታል ነፃ ዝውውር ይኑር፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያሉብን ያከላለል ችግሮች ሠላማዊ በሆነ መንገድ በዘላቂነት ይፈቱ፣ በክልላችን ውስጥ ያሉ ግጭቶችና ጦርነቶች ሠላማዊና ዘላቂ መፍትሄ ይሰጣቸው፣ ቋንቋችን በአስቸኳይ የፌዴራሉ መንግስት ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ይደረግ፣ የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ቢሆኑ በተሻለና ተጨባጭ በሆነ ሁኔታ የኦሮሞ ህዝብ ህይወት በዘላቂነት እንዲለወጥ የሚጠቅሙ ይሆናል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ፍትሃዊ የኦሮሞ ህዝብ ትግልም ሁላችንም አጋር መሆን ይጠበቅብናል፡፡ ወደዚህ ዐይነት ያደገና የበሰለ የትግል አቅጣጫ ለመግባት ግን፣ በቅድሚያ አልጠግብ ባይና ፅንፈኛ የሆነው የወቅቱ የኦሮሞ ብሔርተኞች ስሜት በአግባቡ መስከን አለበት፡፡ ካልተገባ የብሔርተኝነት ፉክክርና እልህ፣ ሁሉን ነገር በጉልበት አማራጭ እፈታዋለሁ ከሚል ትዕቢትና ጉራ፣ ጊዜያዊ ስሜትን ለመቀስቀስ ሲባል የኦሮሞ ህዝብ በአገሪቱ የግንባታ ታሪክ ተሳትፎ እንዳልነበረው መካድና በኢትዮጵያውያን መካከል የቆዬ የህዝብ ትስስርን እንዳልነበረ አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ማንንም ስለማይጠቅም መቆም አለበት፡፡ ስለሆነም በአንድ አገር በእኩልነት አብሮ ለመኖርና የህዝቡን ተጨባጭ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከተፈለገ በአገር ደረጃ የመገንጠልን ጥያቄ፣ በአዲስ አበባ ደረጃ ደግሞ አዲስ አበባን “ፊንፊኔ” ብሎ ከመጥራት ጀምሮ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” አስከሚለው ድረስ ያሉ ህገ-ወጥ እና ምክንያታዊ ያልሆኑ ተያያዥ ጥያቄዎችን እርግፍ አድርጎ መተው ያስፈልጋል፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ከሌላው የአገሪቱ ህዝብ ተለይቶ መብቱ እንዲጓደል የተደረገው በዋናነት የክልልነት ደረጃ እንዳይኖረው በመደረጉ ስለሆነም ህገ-መንግስቱን በማሻሻል የክልልነት ደረጃ እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ አዲስ አበባ የአገሪቱ ርዕሰ-ከተማና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗን ታሳቢ በማድረግም ከተማዋ በአንድ በኩል የአገር ርዕሰ-ከተማነቷን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ራሷን የቻለች ክልል መሆኗን በሚያጣጥም አግባብ በህገ-መንግስት ማሻሻያ እንደገና እንድትደራጅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ #መደምደሚያ በአጠቃላይ- ከአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት የመጣ ህዝብ ከ140 በላይ ለሆኑ ዓመታት ጥሪቱን አፍስሶ በጋራ የገነባትን፣ ከአምስት በላይ የሆኑ ተከታታይ ትውልዶች ተወልደው ያደጉባትን የሚሊዬኖች “አገር” የሆነች ከተማ “የእኛ ብቻ ናት” ብሎ መጠየቅ ከሞራል፣ ከታሪክ፣ ከህግም ሆነ ከፖለቲካ አኳያ ተቀባይነት የሌለው አጀንዳ ነው፡፡ እንኳንስ አዲስ አበባ ራሱ ኦሮሚያ ክልልም የሁሉም የክልሉ ኗሪዎች እንጂ የኦሮሞዎች ብቻ ክልል ሊሆን አይችልም፡፡ በአለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ጋሞዎች በማንነታቸው ተለይተው ሲገደሉ፣ የትግራይ ተወላጆች በጅምላ ከስራ ሲባረሩና ሲታሰሩ፣ አማራዎች ተለይተው ቤታቸው ሲፈርስና ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ ሲታገዱ፣ በአጠቃላይም ኦሮምኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ዜጎች ቤት ሰርተው የማይኖሩበት “ሸገር” የሚባል የከተማ ቀለበት እንዲመሰረትና የአዲስ አበባ ህዝብ በከበባ ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ በገሃድ እያየን ነው። ይህ ሁሉ የሚያሳየን በአዲስ አበባም ሆነ በአገር ደረጃ የኦሮሞ ብሄርተኞች እየፈጠሩት ያለው አደጋ አንድን ብሄር ለይቶ የሚጎዳ ሳይሆን የኦሮሞን ህዝብ ጨምሮ መላውን የአገሪቱን ህዝብ የሚጎዳ መሆኑን ነው። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪካዊ ትስስርና አብሮነት ዋና ቋጠሮ ነች፡፡ ይህ የህልውና የመጨረሻ ቋጠሮ ተፈቶ አገሩ እንዲበተንና፣ በዚያም ምክንያት አገርና ዜግነት የለሽ መሆንን ማንም ህሊና ያለውዜጋና ህዝብ በፀጋ ሊቀበለው አይችልም- አይገባምም፡፡ ከስድስት ሚሊዬን በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ በአግባቡ ከነቃና ከተደራጀ ዛሬ ላይ ጥቅሙንና ህልውናውን ሊያስከብር እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን ችሎ ከ70 በላይ ከሚሆኑት የአለም አገራት የተናጠል ቁጥር የበለጠ የህዝብ ብዛት ያለው በመሆኑ በአግባቡ ከነቃና ከተደራጀ ራሱን በብቃት መከላከል የሚችል ህዝብ ነው። ይህ አቅምና ብቃት ግን በጊዜ ሂደት ሊቀየር እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ ትግሉ ዓላማዬን በዲሞግራፊ ለውጥ ጭምር ማሳካት አለብኝ ብሎ ከሚያምን አጅግ አደገኛና ፅንፈኛ የሆነ ብሄርተኛ ኃይል ጋር ስለሆነ በእንዲህ ዓይነቱ ትግል ጊዜን ቀድሞ መገኘት እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ትውልድ በታሪኩ ከዚህ ጉዳይ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ፣ በጋራ ተባብሮ ሊቆምለትና በጋራም ሊሞትለት የሚገባው ሌላ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ መንግስትና የህግ የበላይነት በአገራችን ቢኖር ኖሮ ሌላውን ሁሉ ትተነው የአዲስ አበባን ህዝብ የውሃ አቅርቦት እናቋርጣለን ብሎ መዛት በአንድ ህዝብ ላይ የዘርማጥፋት ለመፈጸም እንደቀረበ ዛቻና የጦርነት አዋጅ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው ወንጀል ነው። ስለሆነም ጉዳዩ የመላው አገሪቱ ህዝብ የህልውና አደጋ መሆኑን በመገንዘብ “በጊዜ የለንም” ፍጥነት ሁላችንም በጋራ ቁመን በአስቸኳይ ልንታገለው የሚገባ ነው፡፡ ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ ትግል የወረቀት መግለጫ በመስጠት፣ ቁጭ ብሎ በማማረርና የጥቂቶችን ትግል ዳር ቆሞ በመታዘብ ለውጤት ሊበቃ አይችልም፡፡ ተከታታይነት ያለው፣ የተቀናጀና የተደራጀ ሠላማዊ የህዝብ ትግል ማካሄድን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም በስራ ላይ ባሉትም ሆነ አዲስ በሚፈጠሩ ፓርቲዎች ዙሪያ መደራጀትና ከ97 ዓ ም በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች የፖለቲካ ማዕከልነቷን ያጣችው አዲስ አበባ እንደገና ወደ ቀደመ ቦታዋ እንድትመለስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በህገ-ወጥ መንገድ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን ህጋዊ በሆነ ተከታታይ ሠላማዊ ሰልፍና ህዝባዊ እምቢተኝነት መመከት፣ መዋቅራዊ የሆኑ ችግሮችን ደግሞ በምርጫ የፖለቲካ ሂደት የጎላ የትግል ተሳትፎ በማድረግ መለወጥ ይቻላል፡፡ ስለ ምርጫ ፖለቲካ ስናስብም የግድ በየአምስት ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚመጣን አገራዊ ምርጫ መጠበቅ አያስፈልግም፡፡ ተገቢ የሃሳብ ንቃት፣ ተገቢ የትግል ትብብርና አንድነት መፍጠር ከቻልን በእየአንዳንዱ የምርጫ ወረዳ የአስር ሺህ ኑዋሪዎችን የተቃውሞ ፊርማ /Petition/ በማሰባሰብ ብቻ በአዲስ አበባ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህንንም በማድረግ ምንም ዓይነት የኃይል አማራጭን መጠቀም ሳያስፈልግ የወቅቱን የአዲስ አበባን መስተዳድር ፍጹም ሠላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ በወራቶች ውስጥ በምርጫ ማሸነፍና የ1997ቱን ታሪክ መድገም እንችላለን፡፡ እውነተኛና ጠንካራ አማራጭ ኃይል ሆነን ከቀረብንለት የህልውና አደጋውን በግልፅ አያየው ያለው ህዝብ ከጎናችን እንደሚቆም መጠራጠር ዓይገባም፡፡ ከረጅም ጊዜ የትግል ልምዴ በመነሳት በእርግጠኝነት ልናገር የምችለው ከአለፉት 32 ዓመታት በተለዬ መደማመጥ ከቻልን፣ ከአሉቧልታና የሴራ ፖለቲካ ራሳች?
test