ያላለቀ መሳም - /ሶስና አሸናፊ/
Edited by : sosina ashenafi -12/11/2025

እዚህ አነስተኛ የልብስ ፋብሪካ ውስጥ ከተቀጠርኩ ሶስት አመት አልፎኛል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የባህሪም የአቋምም ለውጥ ያላየሁት ሳሮን ላይ ብቻ ነው።

ሳሮን አለቃዋ አፍ ላይ ተቀምጣ ወሬ መልቀም የምትወድ ቀጭን አጭር ሴት ስትሆን፤ማናጀራችን የሚያስተላልፈውን ትእዛዝ ቀልባ ትወረውርልናለች። 

ማናጀራችን ደግሞ ለሱ ያላትን የታመቀ ስሜቷን ለማጋለጥ ወሬውን ጀምሮ ሳይጨርስ ያንጠለጥላታል። በዚህ መሀል ደግሞ ኬሮላይን የሚሏት በኩራት የምትናገርለት የሰውነቷ ክብደት ሚዛኗን የሚሰርቃት ወደእርጅና ላለመሄድ የቻለችውን የምታደርግ ሴት አለች።    

ኬሮላይን የአለቃችን ቅርብ ነኝ ለማለት ይመሥል ድርጊቱን በገብቶኛል ተሽከርክራ ካለይሉኝታ በአሽሙር ትስቃለች። ኬሮላይን እና እኔ ተመሳሳይ የቆዳ ቀለምና ተመሳሳይ የስራ ሀላፊነት ቢኖረንም እሷ ግን እያንዳንዱን የድርጅቱን ስራ አውቃለሁ ባይ እና ለድርጅቱ ተሟጋች ከመሆኗም በላይ ሰራተኛውን የምትፈታተን ለማንም ግድ የሌላት በማያገባት ጉዳይ አፍንጫዋን የምታጠልቅ ነች። የአገልግሎት ዘመኗን ተጠቅማ ለምን ሱፐርቫይዘር አልሆነችም ብልም "መልሱ ፀባይዋ ያስቸግራል" ነው።

እራሷን ሠቅላዋለች። ብዙ አመት መሥራቷ ብቻ ሳይሆን የድርጅቱን ሚስጥር ማወቋም ሌላውን እንድትንቅ አድርጓታል። በዚህ ላይ ጮክ ብሎ መናገርን ጌጧ ያደረገች የስራ ባልደረቦቿን ከደንበኞቿ መለየት የማታውቅ ጋጠወጥ ነች። 

ሳሮን ደግሞ በሱፐርቫይዘርነት የዛሬ አስር አመት በማናጀሩ ተፈትና ተቀጠረች። ይሄንን የነገረችኝ ሳሮን እራሷ ነች። ሳሮን አብረዋት ከሚሠሩት የበላዮቿም ይሁኑ የበታቾቿ አንዲት ነገር በሷ ላይ ቢያደርጉ እጥፍ ብቀላዋን ትጀምራለች። ለዚህ ደግሞ ግንባር ተጠቂ ኬሮላይን ነች። ሳሮን እንደማዳመጥ ብላ አፍንጫዋን ከነፋች አንዱ ሰራተኛ ተደግሶለታል ማለት ነው። በተጨነቀች እና ተንኮል ባሠበች ጊዜ ከንፈሯን ከግራ ወደ ቀኝ በደረቁ ስታሽከረክረውና አይኗ ስር ያለ ሀዘኗን መመልከት ስቃይ ውስጥ ይከተኛል። ቤቷ የምትጋብዘን የእራት ፕሮግራም አላት።ለምን እንደምታዘጋጀው ሳስበው ግራ ይገባኛል። ሁሉም ባለቤት ስለሚሆን ግብዣው ላይ መገኘትም ሞቴ ነው። ግን አይቀርልኝም። በተለይ ኬሮላይን ደግ ነኝ ባይና አለቃዋ እንደሆነች እንኳን ማሰብ የማትፈልገዋን ነፍሴ ትጠየፋታለች። በዚህ ልክ መሆን ይቻላል ? እላለሁ። እንደሁለቱ መውደድ መጥላት፣መሆን አለመሆን?መቅረብ ደግሞ ማራቅ የኑሮ አባባይ መሆን? ማንሳት መጣል? በየቀኑ ልዩነትን አስፍቶ ደግሞ ለማጥበብ ፍዳ መብላት፤ ይሄን ነው ያየሁት። 

ኬሮላይን ለሰላሳ ሰባት አመት በድርጅቱ ማገልገሏን እና ከሌላው ሰራተኛ መብለጧን መለኪያ አድርጋ ለመጣ ለሄደው ሠራተኛም ሆነ ደንበኛ ማስረዳት እንዲሁም  

የገዘፈ ሰውነቷ መሬት እንዳይነካ ቤቱን በእርዱኝ ጩኸት ብዙ ጊዜ ማድመቋ ግድ ነው እላለሁ በትዝብት እያየኋት።ከዚህ ቀደም ወድቃ በመሠበሯ ከስድስት ወር በላይ ከሥራ ቀርታለች። ለመውደቋ ደግሞ ሳሮን አስተዋፅኦ አድርጋለች ባይ ነች። ግን የሳሮን የእራት ግብዣ ላይ ዋና ባለጉዳይ ለመሆን ወደኋላ አትልም። የእራት ጥሪ የሚያስተላልፈው ማናጀራችን ባይሆን ኬሮላይን ከፍ ዝቅ በማድረግ ሌላ ጊዜ እንደምታደርገው ትጫወትብን ነበር። በግብዣው እለት ተጠርቶ መቅረት የማይችለው ራት ተጋባዡ ሰራተኛ ሳይፈልግ የሁለቱን ፉክክር ይጠጣታል። ከቻለም እንደኔ አንዴ ከአንዷ ሀሳብ ሌላ ጊዜ ከሌላዋ አስተያየት ላይ እየወደቀ የተቸገረውን ማናጀር አይቶ እንዳላየ ለማለፍ ይሞክራል ።

"መጠጡ በኔ ነው "ይላል ማናጀሩ አስቀድሞ

"ምንም አያስፈልግም እናንተ ብቻ በሰአታችሁ ተገኙ" ትላለች ሳሮን።

ምግቡን ከአፍ እስከገደፉ በሻንጣ ሞልታ የምትመጣው ደግሞ ኬሮላይን ነች።

ስድስት አመት ያሳለፉት እንደዚህ መሆኑን በመቀባበል ማናጀራችን እረፍት በሚወጣና እነሱም ውሀ እንጥበስ ያሉ ቀን ያወሩታል። 

ዛሬ ግን ሰባተኛው ሳምንታዊ የእራት ግቡብዣ ጥሪ እንዳልተደረገ ከኔ ቀድመው የገቡት የስራ ባልደረቦቼ ሲያወሩ ሰማሁ። የኬሮላይን ሳቅም አልተሰማኝም።

ማሰብ ጀመርኩ። 

ያየሁትን እና ያደረኩትን ያዩ ይኖሩ ይሆን እንዴ? 

ብቻ ገና ከመግባቴ ሳሮን አይኗን እንደቢራቢሮ እያርገበገበች እኔና አንተ እያለች እንደሁል ጊዜው የስራ መአት ጫነችብኝ። ማናጀሩ ተከትሏት ገብቶ አፈጠጠብኝ። ደነገጥኩ። ከዚህ ቀደም ያየሁትን ሊስማት ጀምሮ ያልጨረሰውን ለማንም አላወራሁም። 

ነገሩ የሆነው ድንገት ነው። የስራ መግቢያ ሰአቴን ልቀይር ወደቢሮ ሳመራ የእቃ ማስቀመጫ አነስተኛ ክፍል ውስጥ ቆመዋል። ልግባ አልግባ በሚል ሳመነታ ከንፈሯን ነክሶ ሲለቃት አየሁ። የጀመረውን ለመጨረስ እና ከንፈሩን ለማግኘት ስትቃትት ጥሏት ወደእሱ ቢሮ በሚወስደው የውስጥ በር ወጣ። እንባዋ እንደተንጠለጠለ ዞር ስትል አየችኝና በምልክት ጠራችኝ እና ክፍሉን ዘጋችው። ቅጥነቷን ብወደውም እሷ ላሰበችው የተጣደፈ ነገር አልተዘጋጀሁም ነበር። ብቻ የሆነው ሆኖ በሩን ልትከፍትልኝ ስትጣደፍ ደግሜ ድብን አድርጌ ሳምኳት። በደስታ እኔ ላይ ተጠምጥማ አለቀሰች። ያለቀሰችውንም ሆነ የሆነውን ለማንም ተንፍሼ አላውቅም። እሷም ከዚያ ወዲህ እንደታናሽ ወንድሟ በስራዬ በማገኘው ጥቅማ ጥቅም ታግዘኛለች። 

ማናጀራችን ግን የሠራነውን ስራ እንዳወቀብን ያወኩት ዛሬ ነበር። 

"እሱ ከእኔ ጋር እታች ይውረድ "አላት

"ግድ የለም እሱ ከኔ ጋር ይሆናል" አለች

ሳይወድ ጥርሱን ነክሶብኝ ሄደ።

ፈራሁት። በቅርብ የምትሞት እናት ስላለችኝ ከስራዬ መውጣት አልፈልግም። ይሄንን ደግሞ ሳሮን አስረድታዋለች። "የምታግዢው ለዚህ ነው ለካ?" ሲላት በምፀት

" አዎን" ብላ በድፍረት መልሳለች። 

"ሰማህ ያቺ ቢች ከእንግዲህ አትመጣም የሷን ቦታ እንሸፍናለን" አለችኝ ወደላይ እየወጣን።

"ማ!" አልኳት ባውቅም እንዳላወቀ ሆኜ ምክንያቱን ለማወቅ።

"ኬሮላይን" አለችኝ ሌላዋ ባልደረባዬ

"ምን?" አልኩ ባለማመን።

"ማንም አልሰማም" አለች ሳሮን

"ምኑን" አልኳተት

"መባረሯን"አለች የኔ መደንገጥና ግራ መጋባት ጥያቄ ፈጥሮባት።

"አዎን ሱፐርቫይዘር ማባረር ይችላል እንዴ?" ስላት

"ከማናጀሩ ጋር ተጣልታ ነው" አለች

"እንዴት?" አልኳት

"በደንበኞች ፊት ተናገረችው ሰደበችው ማለት ይቀላል"

"እሱን?" አልኩ እልኸኛነቱን አስቤ 

"አዎን በእኔ የለመደችውን"አለች በሳቅ ተሞልታ። ከዚያ "እንደኔ ታጋሽ ይመሥላታል ሁለም። አገኘችዋ!" አለች

"ሀያ ሰባት አመት ገደል?" አልኩኝ ሳይታወቀኝ።

"ማንም ሰው እንደዚያ ነውስርአቱን ካልያዘ" አለ ማናጀሩ

ለካ ከኋላችን ተከትሎናል ። ፍርሀት ሰውነቴን ወረረኝ።

test