ሠማያዊው ወንበር /ሶስና አሸናፊ/
Edited by : addiskignit@gmail.com -12/22/2022
የሚወርደውን ቅዝቃዜና ንፋሳማ ዝናብ ለማምለጥ ከቆመው ባስ ውስጥ ገባሁ። ቀኑ ሲያስጠላ እኔ ዝናባማ ቀን አልወድም ጩህ ፣ አልቅስ ፣ ለፍልፍ ይለኛል። ዛሬም እንዲሁ ሆኛለሁ። ውስጤ የሚሞግተኝን የኩሊነት እና የአይረቤነት ስሜት ለመሸሽ የከፈትኩትን ሙዚቃ ጆሮዬ ላይ እያስጮህኩ መቀመጫ ፍለጋ አይኔን ወረወርኩ። ቀዩ መቀመጫ ተይዟል። ደግሞ ጉልበቴ በድካም ዝሏል። ለምን ሠማያዊው ላይ አልቀመጥም ? ሁል ጊዜ ህግና ደንብ ከማክበር አንዳንዴ መጣስ ምን አለበት ? የሚል የድጋፍ ሀሳብ ከውስጤ አበረታኝ እና ተቀመጥኩ፣ ተመቻቸሁ ረጅም መንገድ ለመሄድ አቅጄ ጨረስኩ። አንዳንዴ እንደገባሁ መቀመጫውና ሁኔታው ከተመቸኝ መንገዴን እቀጥላለሁ። ከጫፍ እስከጫፍ ስመላለስ እዛው ተኝቼ እንቅልፌን ጨርሼ ነቃለሁ። እስኪ አሁን ካልጠፋ ነገር ሰማያዊ መቀመጫው የአዛውንት ፣የልጆችና የደካሞች ቀዩ ደግሞ የሴቶች የወንዶች፣የሁለቱም ፣የመካከለኛ እድሜ እና የሌሎችም. . . ብሎ በህግ ማሠር ምን ይሉታል? ደጋግሜ ጠየኩ። ከራሴ ጋር በማይረባ ነገር ስተራመስ የመጀመሪያውን ዘፈን ሳልሰማው አለቀ። ሁል ጊዜም እንዲህ ነኝ። ጆሮዬ ላይ ከመጮህ ሌላ ይሄ ነው ብዬ ሳልይዘው ቤቴ ደርሳለሁ። "ይቅርታ ባለወንበሯ መታለች እዛ ጋር ትቀመጥ?" ሲለኝ የባሡ ሹፌር. . ቂጤን በመርፌ እንደተወጋሁ ተስፈንጥሬ ስነሳ የወንበሯ ባለቤት ዊልቸሯን እያሽከረከረች በኩራት ስትገባ አይን ለአይን ተገጣጠምን። ሰማያዊ አይን በቀይ ከንፈር!! ቀጥ ብሎ የወረደ አፍንጫ፣ ከኮፍያ አምልጦ የወጣ ወርቃማ ፀጉር። ሰማያዊው ወንበር ታጥፎ ቦታዋን ስትይዝ አብሯት የነበረው ሰው ጀርባዋን አሻሽቶ ግንባሯን ሳማት። ልጁ ነች ሚስቱ? እድሜያቸውን ለመገመት አልቻልኩም ቅዝቃዜው የፊታቸውን ቆዳ አንጥቶ መጦታል። ልጁ እንዳልሆነች አወኩ። የልጅና የአባት ሁኔታ አላየሁም። ከዊልቸሩ ኪስ " Making love " የሚል መፀሀፍ አወጣች። አይኔም አፌም እኩል ተከፈተ። በረጃጅም ጣቶቿ መፀሀፉን ገልጣ ከንፈሯን መጠጠች። ምን ሆና ይሆን? እንደኔ ፍዳዋን ስትበላ ክልትው ብላ ይሆናላ ማን ያውቃል? አልኩ ለምን አልጠይቃትም? ከዛ የሆነችውን እሰማለሁ። ግን ደግሞ ምን አገባኝ? ከመጠየቅ ብዙ ነገር ይገኛላ! ወይ ጉድ እሱ ድሮ ቀረ። አሁን መዘዝ ይዞብኝ ቢመጣስ? ከራሴ ጋር ስሟገት ለካ አስር ፌርማታ ሄደናል። ወደቤቴ የሚወስደኝን ባቡር የምይዝበትን ፌርማታን አለፍኩት። ስንከረፈፍ አብረውኝ የተሳፈሩት ወርደው በሌሎች ተተክተዋል። "ዋው" አለች ለሶስተኛ ጊዜ የምታነበውን መፀሀፍ ከአንዱ ገፅ ወደሌላው ስትሻገር ሰውየው አሁንም ጀርባዋን ደባብሶ ግንባሯን ሳማት ለምን ከንፈሯን አይስማትም?❤️ ሹፌሩ መንገድ እንድንለቅ ተናግሮ በሩን ከፈተ "መልካም ቀን" ብላኝ ዊልቸሯን እያሽከረከረች ከባሡ ወረደች።
test