Stories & Essays

ህይወት አልባው የስደት ሽኩቻ!!

Gezahegn Mekonnen Demissie·
Share
- ሶስና አሸናፊ


- ሶስና አሸናፊ

መሥሪያ ቤቱ ከወትሮው በተለየ በባለጉዳይ ተጨናንቋል።

መሥሪያ ቤቱ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሲወድቅ ኢቭ የሱፐርቫይዘር ስራዋን ትጠላዋለች። በዚህ ላይ ለእያንዳንዱ ሰራተኛ ስትረሷን ማጋባት ትወዳለች። ዛሬ አብረናት ያለነው እኔና ሉዊስ ነን። አጋጣሚ ዋሽሩም ደርሳ እስክትመለሥ ሉዊስ ስስ ከንፈሩን አሞጥሙጦ

"ኢቭ የውሸት ኑሮ እንደምትኖር ታውቂያለሽ? ሁሉ ነገሯ ፌክ ነው። "አለኝ

ከሱ ጋ ማውራት አልወድም። ሀሜቱ መቀመቅ ይከተኛል። መልስ ሳልሰጥ ዝም አልኩት እያየሁት። "She is fake" አለኝ ደገመና። ሉዊስ ቀጭን መካከለኛ እድሜ ያለዉ የስራ ጫማውን ክብደት መቋቋም አቅቶት እየጎተተ የሚሄድ እራሱን በማናጀር ቦታ የሚቆጥር ዘባራቂ ፣ ቅጥነቱ እድሜውን የዋጠበት የአእምሮ ጤናውን በካናዳ ኑሮ እያጣ የመጣ ከርታታ ነው።

"ልጅ የላት፣ባል የላት፣ቦይፍሬንድ እንኳን የላትም።ከዚህ ውጭ ህይወት እውነት ይመሥልሻል? አታጨስ፣ አትጠጣ" አለ ደገመና። በጣም ደነገጥኩ። ግን መልስ አልሰጠሁም።

ኢቭ ከሄደችበት ተመለሠች።

 አይኗን ላለማየት እቃ መሠብሠብ ጀመርኩ።

"ምን እያወራህ ነው?" አለችው። እኔን እያየች። እኔ ግን ባልገባኝ ዝም አልኩ።

ትንንሽ የድመት አይኖቿን አፈጠጠች። እንኳን ስለእሷ ተወርቶ ንፋስ በዚህ በኩል አልፏል ባይ ጠርጣራ ናት።

ሁለቱም በቂም ተያይዘዋል። እሱ እንዴት በሴት እታዘዛለሁ በሚል እና "የኢንጂነርነት ክብሬ ተነክቷል እሷ ንቃኛለች።"ባይ ነው።

እሷ ደግሞ "ሳይሰሩ መብላት የለም።" አለች። ኢቭ ጠበቅና ረገጥ አድርጋ። ሉዊስ እና ማናጀሯ የአገር ልጆች ናቸው። ኢቭ ግን ነገሯ ከሰው የማይገጥም ቢመስልም ነገሮችን ታመዛዝናለች። ሉዊስ አንድ ስራ ከሰራ ሌላውን ሰአት በወሬ ይጨርሰዋል። በዚህ ላይ የእያንዳንዱን ሰራተኛ የእግር አጣጣል መዝግቦ ለማናጀሯ ያቀርባል።

ኢቭ ደግሞ በእኔ የስራ ሰአት ወሬ ለምን ታቀብላለህ ባይ ነች ። ደግሞ የተናቀች አይምሰላትእንጂ ከመሠላት ግን እስከጫፍ ለመሄድ አትመለሥም። ማስረጃ ቆጥራ ሶስት የተፈታተኗትን አባራለች። “እኔ እምታወቀው ማንኛችን ቤት የችግር ማእበል እንደሚናጥ ስለማታውቁ ከሥራ አታባሩ በሚል ነው።” ኢቭ ግን በስትረስ የተበጫጨቀው አካሏ እስኪንቀጠቀጥ ተናግራና ወንጅላ አታቆምም።

"ትሰሚያለሽ ኢቭ ! ለምን እንደዚያ እንዳልኩሽ ገብቶሻል?"አላት በእልህ ቀጭን አንገቱን ወደጎን አዘንብሎ።

"አልገባኝም። እንዲገባኝም አልፈልግም። እኔ የምፈልገው ሥራህን እንድትሰራ ብቻ ነው" ብላ ሳትጨርስ ጣልቃ ገብቼ" እሱ የተናገረው የከስተመርን ጉዳይ ነው።" አልኩ ፍርሀት ይዞኛል።

" አንቺ እኮ አልነበርሽም ስናወራ።" አለችና ልደብቀው ያለ ነገር መኖሩን በቆልማማ አፍንጫዋ ማሽተት ጀመረች።

"እኮ ስለማታውቂው እኮ ነው።" አላት

"What do you mean?" አለች

"ኑሮን ለመረዳት በጣም ወሳኝ ነው ያልኩት ነገር" አለ በድፍረት

"ምኑን ?"አለች ለፋሽን የመለጠችውን ጭንቅላቷን በንዴት እያሸች።

"ለምን አትነግሪያትም ሰላም?" አለኝ። የጀርባዬ አገዳ ለሁለት የተከፈለ መሠለኝ። እንደዚህ ያደርገኛል ብዬ አልገመትኩም ። ትንፋሼን ከቦታው አጣሁት። ለክፉ ነገር ምስክር እንደመሆን መርገምት የለም አልኩ ለእራሴ።

አይኗ ከቦታው የተነቃነቀ መሠለኝ። ጥቁር አይኗ በእጥፍ ጨምሮ ደምቆና ወደውጭ ፈጦ ታየኝ።

"ማ!" አልኩት ደርቄ እና ድምፄን አጉልቼ።

ኢቭ በቅፅበት ልታደርግ ያሠበችውን ሲረዳ ሉዊስ አንገቱን አቀረቀረና ጥሎን ሄደ።

"You know? ምን ለማለት እንደፈለገ ገብቶሻል?" በሰው መላከክ ይፈልጋል። " አልኳት በደፈናው።

"I know I know እንግዲህ ይታያል Nightmare ይሆንበታል" አለች የስልክ እጀታውን እያነሳች። ያለማቋረጥ አስራአምስት ደቂቃ ለፈለፈችላት።

ማናጀሯ ቁና ቁና እየተነፈሰች መጣች።

"ምን ተፈጠረ ? አለች። እኔን መሥካሪ አድርጋ።

"ምን " አልኳት ጥያቄዋን ወደራሷ መልሼ።

እኔ ለእራሴ በአሥራ አምስት ዓመት የሥደት ቆይታዬ የአኗኗሩንም የመበላለቱንም፣ አንዱ ሌላውን የመወንጀሉንም የማጥፋቱንም አውቄ ተውጬ እየተተፋሁ መኖር ችዬበታለሁ። የራሴ የሆነውን ሰው ሳይቀር ገበናውን ገልጬ አይቻለሁ ። እየሸነገሉ ማጥፋትን አይቻለሁ።

"ትሰሚያለሽ I can’t. I’m tired of dealing with him. He doesn’t do anything, so I’m waiting for your decision. Come on. " አለች ኢቭ የክስ ወረቀቷን እያውለበለበች።

ማናጀሯ ግራ በመጋባት ውስጥ ሆና አየቻት።

አላውቅም በሚል አንገቴን በምልክት አሳየኋት ባትጠይቀኝም።

"ዛሬ አንድ ነገር ካላደረግሽ ዋናው ቦታ እፅፋለሁ።"

አለች። ጥያቸው ባለጉዳይ ለማናገር ሄድኩ። ዛሬ

ማናጀሯ ባለችበት ብትጠራውም ሉዊስ ግን

መልስ አልሰጠም። በእጄ ምልክት ሰጠሁት። እሱም በእጁ የንቀት ምልክት ሲያሳይ ሁለቱም አይን ውስጥ ገባ።

"ቢሮ አናግረዋለሁ" አለች ማናጀሯ

"እዚሁ አድርጊው ። ጉዳዩ የተፈፀመው እዚህ ነው። አለች"ኢቭ የማናጀርነቷን ስልጣን በሉዊስ ላይ ለመጠቀም እየፈለገች።

"ባለጉዳይ ፊት?" ማናጀሯ ግራ በመጋባት ጠየቀቻት።

"ጥፋቱ የተፈፀመው እዚህ አይደል?"

ማናጀሯ የደንበኞችን ትኩረት ላለመሳብ እንደተወናበደች እየሳቀች ጠራችው።

እንደለመደው ጫማውን እየጎተተ መጣ። አይኑ ቀልቷል። አፍንጫው ወርዝቷል።ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠ ምን ምን" አላት ወደ ሱፐር ቫይዘሯ ኢቭ እያየ።

"ለምን አልታዘዝክም? የአንተ አቤቱታ በዛብኝ።" አለች በሁለቱ መሀል ሆና።

"እንደውም ልንገርሽ " አለ የሱፐርቫይዘሮችን ጠረጴዛ ተደግፎ።

"የህይወትን ጣዕሙን አታውቅም። ለዚህ ነው ወጣ ገባ ሄደ መጣ የምትለው። እኔ እሩቅ ነው የማስበው ልጅ መውለድ ቤተሠብ መምራት. . እፈልጋለሁ።

ቤተሠብ ደግሞ ለባህሪሽ ወሳኝ ነው። እሷ ግን ኔቨር ኔቨር. . .መቼም አታገኘውም " አለ ጤነኛ በማይመሥል ድምፅ በሳቅ አጅቦ።

ሉዊስ ብቸኛ እንደሆነ እና ለማግባት ቢፈልግም አቅም እንደሌለው ፣ ወረቀቱን ቢያገኝም ወደሀገሩ መመለስ እንደሚፈልግ አውርቶኛል። ተባሮ ሆምለስ ቅርጫት ውስጥ ለመግባት ምን እንዳጣደፈው ሳስብ ይበልጥ ፈራሁት።

የሠውነቱ ያለመታጠብ ጠረን አካባቢውን ሞላው።

ኢቭ ግን የያዘችውን እስክሪብቶና ወረቀት በንዴት ወርውራ ጠረጴዛው ስር ስትወድቅ የዲስትሪክት ማናጀሩ ሲደርስ እኩል ገጠመ።