የሀዘን ልቃቂት /ሶስና አሸናፊ/
Edited by : Gezahegn Mekonnen Demissie -10/21/2023
"በሀዘን ልቡ የተመታን ሠው ፊት እንደማየት ከባድ ነገር የለም። ተስፋ መቁረጡና አንገት መድፋቱ ልብን ከፍሎና ሠቅዞ ይይዛል። " አለች ሚሚ እንባ ባቀረሩ አይኖቿ እያባበለችኝ። "ምን ገጠመሽ?" አልኳት። እንዲሁ ሲፈጥራት ሀዘን ላይ የጣላት ነች። አንድ ነገር ፈልጋ እንደተለማመጠችኝ ጠርጥሬያለሁ። "ለምንድነው አንዳንድ ሀዘን ከልብ ውስጥ ገብቶ የሚተከለው ?" አለች። "አንቺ ፍቅር ያዘሽ እንዴ? ዋ ያለሽው ሰው ሀገር ነው" አልኳት "አረ በፍፁም ከማን?" አለች አይኗን እያንከባለለች። " እንዴት ከማን ከሰው ነዋ!" አልኳት ቆጣ ብዬ። "ጊዜ ሲኖር ነዋ! እኔ አቧራ አንፋሽ!! በምን ጊዜዬ" አለች አፍንጫዋ ላይ የሰካችውን የብረት ጌጥ እንደመጥረግ እየነካካች። ጌጡ ለሷ ብቻ የተፈቀደ ይመስል ያምርባታል። " ከአይሆንም ይሆናልን እያሠብሽ! ራስሽን ጠብቂ እሺ"!"አልኳት "ወድጄ ነው። እልቅ ለነገ ልለምንሽ ነው የመጣሁት" " ስራ ቅሪ እንዳትይኝ አላደርገውም" አልኳት። "ስሞትልሽ ያሳዝናል እንሂድለት" "የት? " "እሱ ጋር ብታይው አንቺም ታዝኚያለሽ" " አንቺ ?. . ማነው እሱ?" ባልነግራትም ደንግጫለሁ። "ስታይው ይገባሻል!" አለች "ለማላውቀው ሰው አላደርገውም በጭራሽ! አጨሰብሽ እንዴ?" አልኳት። እሷ ግን አልሰማችኝም። "ባለፈው ያምራል ያልሽው ሙዚቀኛ ነው?" ጠየኳት መልስ አልሰጠችኝም። "ደራሲው?" "አንገቷን በአዎንታ ነቀነቀች። "ደራሲነት እኮ እዚህ አያዋጣም ማን ያነባል? የገሀዱ አለም ነፀብራቅ ነው ቢልም እጁ እስኪዝል ቢፅፍም ዲያስፖራው አላነብም ጊዜ የለኝም ብሏል።" አልኳት ሆዷ እንዲቆርጥ። " ስደተኛ ወይም ጥቁር ስትሆኚ ነዋ!" አለት እልህ ባፈነው ድምፅ "ምንም የትም ቢሆን የተረገመ ነው ድርሰት። ስደተኛ ብትሆኚ የራስሽ ሰው ታጫለሽ? ቋንቋሽን የሚያውቅ የሚችል? ማንም ቦታ አይሰጥሽም ባክሽ ወገንሽም ከጉዳይ አይጥፍሽ ዝም ብለሽ አቧራሽን አንፍሽ" አልኳት። ለኪነጥበብ ያላትን ፍቅር ስለማውቅ እርሟን እንድታወጣና ሆዷ እንዲቆርጥ። ገረመመችኝና ረጃጅም ጥፍሮቿን ውብ ከንፈሯ ላይ ጠረገችው። ከዚያ "አንቺ" አለችኝ በመታዘብም በመጠየቅም ስሜት "እንኳን ዘፈኑንና ዘፋኝ ወደድሻ!? ወደው መሠለሽ እንዴ በየስቴሽኑ ቅርጫት አስቀምጠው የሚዘፍኑት? እንዳንቺ መሥማት የሚወድ የሚያንጎራጉር ሩህሩህ ልብ ያለው ተመልካችና አድማጭ እንደሚያገኙ ገብቷቸው ነው። " "ሰው ግን ምን አይነት ነው?"አለች በመከፋት "ጊዜ የለውማ ምን ያድርግ" አልኳት " እንዴ ለሌላ ነገር ተሰልፎ አይቻለኋ! ሲጋፉ !! ለኪነጥበብ ግን . . " የጀመረችውን ሳትጨርስ ተወችው። "ምን ይሰራል ኪነጥበብ ለራሡ ያልሆነ።" አልኳት ጨክኜ " .በቃ ዛሬ እንሂድ ስሞትልሽ?" አንገቴን አቅፋ ለመነችኝ። ሄድን . . . በከተማው ካለ አንድ ታዋቂ ህንፃ ውስጥ ገባን። አዳራሹ ሰፊ ቢሆንም ሶስት አራት ወንበሮች ብቻ በሰው ተይዘዋል። ሚሚ ካለእረፍት ስለደራሲው ድካምና ስለወሠደበት ጊዜ የምረቃው ስነ ስርአት ላይ የተጠሩት እንግዶች አለመገኘታቸውን ባለመምጣታቸው ደግሞ የተሠማውን ባዶነት ከራሷው የተጋነነ አስተያየት ጋር ጨምራ እየጋተች ፋታ ነሳችኝ። " እውነታቸውን ነው አልኳት ሰው እስኪመጣ ያጠፋነውን አንድ ሰአት ወደገንዘብ እየቀየርኩት። "ምግብስ?" አለች ተበሳጭታ "እሱማ ከወጪ ይገላግለኛላ! እዚህ ከበላሁ ቤት መሥራት አይጠበቅብኝም።" አልኳት በድፍረት እየሳኩ "ሁል ጊዜ እንደሡ አትኖሪማ" አለች ተጠይፋኝ ። የእጅ ሠአቴን አየሁ። ሁለት ሰአት ሊሞላ የቀረው ጥቂት ነው አልኳት ላለመበገር። ሁለት ሰዎች ተጨመሩ። በድምሩ ከአስራ አምስት አንበልጥም። ደራሲው ቁና ቁና እየተነፈሰ ቲያትሩን ለመድረክ ለማብቃት እና ወደህዝብ ፊት ለማድረስ የፈጀበትን ሁለት አመት ሲናገር ድምፁ ወደውስጥ እየተሳበ በተስፋ መቁረጥ ከእድሜው መቀነሱን ያሳብቃል። "ምን እዳ መጣበት ቢቀርስ ሠው እየሠራ እንደሚኖረው አይኖርም? ምን ጣጣ ውስጥ ዘፈቀው?" አልኩ ተናድጄ። እውነትም የደራሲው ሁኔታ ልብ ይሰልባል። "ጥቁር ስለሆነ ይሆናል ምናልባት እንዴት አለቃው እንኳን ይቀራል?" "እንጃ! ጓደኞቹስ እንደው አንድ ሀያ ጓደኛ ያጣል ? ሀምሳው ይቅር ። ደግሞ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው ብሏል ወይ የገሀዱ አለም ነፀብራቅ . . . !! የራሡ ታሪክ ይሆን እንዴ?" አልኳት ሴቷ ተዋናይት ድምፀ መረዋ እንደሚሏት አይነት ነች። መድረኩ በሁለቱ ብቻ ደምቋል። ምናልባት ፍቅረኛሞች በመሆናቸው ይሆናል። "ወንዱ ጎበዝ አይደል? ሲስማት የእውነት አስመስሎታል።" አለች "ታዲያ ቲያትረኛ መምሰል ሳይሆን መሆን አይደል?" ራሷን ጠየኳት "ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ መታየቱ ነው። ገንዘቡ ይቅር ድካሙና ሞራሉ በምን ይካሳል? የራስ ወገን ይጠፋል? ጓደኞቹ ቢከቡት ምናለ የሀገሩ ሠዎች " "ሴትዮ አትሠሚም እንዴ እናት የለኝ አባት የለኝ ብቻዬን ነኝ ሲል? ደግሞስ ሀገሩ እንኳን ለጓደኛ ለባልና ሚስት ደባል መሆኑን ረሣሽ ? ተኛ ነጋ ወጣ ሴትዮ አመረርሽው ኦኮ! መቼም አንቺ እንዲ ከተንገበገብሽ እሱ ነፍሯላ?!" ንግግሬን ሳልጨርስ ደራሲው ደበሎ ሆዱን እያንከቤለለ አጠገባችን ደርሷል። እቅፍ አርጎ በባለውለታነትና በወገን ስሜት ስሞ ሲያመሠግነን የእድሜውን መገባደድና ተስፋውን ከሚስቁት ትንንሽ አይኖቹ ላይ አነበብኩ። በሀዘን የተሸማቀቀው ልቤ ሲፍታታ ተሠማኝ። Oct 11/2023
test