"ይሉሽን በሰማሽ አሉ.."/ሶስና አሸናፊ
Edited by : sosina ashenafi -11/18/2023
"አንቺ በተወደደ ኑሮና በጠፋ ስራ አርፍደሽ ትመጫለሽ አልኳት የስራ ባልደረባዬን ። ነገር ስትይዝ ታምረኛለች። ድብልብል ሰውነቷና ወፍራም ፊቷ ሳቅ ጨምሮ ይበልጥ ይሰፋል። "ወይ ጉድ እሳት ላይ እንደቆየሁ ብታውቂ፣ ስንት ጉድ አለ አንቺ ወይ ጉድ በማላውቀው ነገር ተጠብሼልሽ፣ እስኪ በይሉኝታ ማን ተጠፈሪ አለኝ ምንም ለማልፈይደው" አለች በማውራት ሳይሆን በማጉረምረም ። ሠውነቷን እየሠበቀች። "ምን ተፈጠረ?" አልኳት "ይኸውልሽ . . "አለችኝ ሽርጧን እየቋጠረች። " እናንተ ምን ጉዶች ናችሁ? እንዴት የምትኖሩበትን ሀገር አናውቅም ትላላችሁ?" አለኝ " እኔን ነው " በሚል አየሁት። ረዘም ቀጠን ያለ ነው። ሰብዌ መግቢያው ላይ እሱ ሲወጣ እኔ ስገባ ነው የተገናኘነው " ገንዘብ አልተጠየቃችሁ የተጠየቃችሁት ቦታ አሳዩኝ ነው የተባላችሁት ፣ እኔንጃ ሌላ ሰው ጠይቅ ነው መልሳችሁ። ከአንዳችሁ አንዳችሁ አትሻሉም። ይሄንን ከምቀኝነት ለይተንና ነጥለን አናየውም" አለ ። ቀጠለና "እናንተ በመሀበር ስም በዘመድ አዝማድ ትሠራላችሁ? ትጠቃቀማላችሁ? ከዚያ ድረስ መጥታችሁ? ኧረ እፈሩ ለየትኛው ጊዜ ብላችሁ ነው?"። አየሁትና ሸሸት እንደማለት አፈገፈኩ። "ኢትዮጵያዊ ነሽ አይደል?" አለ ኢትዮጵያ ማለቱ ገርሞኝ አዎን ነኝ አልኩት። ሀበሻ ነሽ ነው እዚህ በብዛት ጥያቄው። "ምነው ታዲያ ዝም አልሽ? ገና ምንም አትለወጡም? እንደዚያው ናችሁ እንደሀገር ቤት?አሁንም በዘመድ ስራ ታስቀጥራላችሁ?" አለ ወደጓደኞቹ እያየ። "ካናዳ ደግሞ በዘመድ የሚባል ነገር አለ እንዴ?" አልኩት ቅዝቃዜውን ለማምለጥ አፌን በሻርቤ እየሸፈንኩ። " እንዴ አየን እኮ አየነው የዘመድ አዝማዱንማ!! እኛ ዘመድ የሌለንስ?" አለ። "እግዚሀር ነው ዘመዳችን ባክህ" አለ ሌላው "አበሻ ቤት ከሆነ ራሣችሁ አትጠይቁም?" አልኩ ተናድጃለሁ። "ማን አድርሶን አንዳንዱ ያወራል እንጂ አያቀርብሽም። እንድታጅቢው ወይም እንድታሞቂለት ይፈልጋል። ደግሞ እንዲህ አድርጌያለሁ ብሎ ጉራውን ሊቸረችርብሽ ይነሳል። አንድቀን አብልቶ. . ኧረ ተይኝ የናንተ ነገር ተወርቶም አያልቅ " ሲል ፤ ሌላው ቀጠለ " "ማን ምን እንዳለው አውቀን?" "ስንት ጊዜ ሆናችሁ?" አልኩ "ሶስት ወር አልፎናል። የስራ ፈቃድ አግኝቻለሁ" አለ አንደኛው "እየለመዳችሁ ነዋ!?" አልኩ አፌ ላይ የመጣልኝን "በሰቡኤ መምጣት መሄድ ችለናል" "ታገሡ ዊንተሩ ይለፍላችሁ" "እስከዛ እንሙት?" ሌላው ቀጠለ "ግን አታፍሩም?" አጠር ወፈር ያለው አከለ "እንዴት??" አልኩ ግራ በመጋባት "ምን እንዴት ትያለሽ መሀበር መሥርታችሁ በዘመድና በመተዋወቅ እየሠራችሁ ሆድ መሙላት ምን ይረባል ከሠአት ይርበናል ማታ ምግብ ያስፈልገናል። " "የምን መሀበር ነው የምታወራው አልኩት" መሀበርም መሀበር ውስጥም ስለሌለሁበት። "መሀበር ነዋ መሀበር አታውቂም?" "መልክ ተምታቶብህ ይሆናል። ግን ለምታወራው ነገር ደግሞ ማስረጃ መያዝ ግድ ነው። ዝም ተብሎ አይዘረጠጥም" አልኩት። ይሄኔ የተከናነበውን ከፊቱ ላይ ገልጦ "ማስረጃ ትፈልጊያለሽ ብሎ ዘረዘረው። ጠይም ነው በሀያዎቹ መጨረሻ የሚገመት። እሱ ብቻም አይደለም አምስት ይሆናሉ ጓደኞቹ ፤ አንዴ በመሣቅ አንዴ በመደገፍ አንዴ ደግሞ በማሽሟጠጥ ፣ አንዴ በመታዘብ አንዴ ሀሳብ በማዋጣት ፤ አንዴ ጭልጥ ብሎ በሀሳብ በመሄድ፣ መለስ ብለው በመደናገር ጓደኛቸውን ያጅቡታል። ድንገት "እናንተ ምነው ዘጋችሁኝ እናንተ ጋር ለመድረስ አለከለኩኝ።" አለች። ቀጭን ፀይም ፀጉሯን በአጭር የተቆረጠች ነች። ሰአቴን አየት አድርጌ ከቆምኩበት ተንቀሳቀስኩ። " አንቺው ነሽ እንዴ ጠፋሽን እኮ ባለፈው እንደዚህ አልነበርሽም" አላት "እንዴ ማን ይሞታል ቆረጥኩታ ለራሴ ግራ ተጋብቻለሁ ለፀጉሬ መሠሪያ ደግሞ ላስብ?" "አብረሻቸው ነሽ?" አልኳት ለመገላገል ፈፈልጌ "አይ መሀበሩ ጋር ስሄድ ተዋውቄያቸው ነው ምስራቅ እባላለሁ።" እጇን ዘረጋችልኝ። አልጋነሽ ነገርኳት። "እሷ ነች እንዴ ስራ የምትጠይቅላችሁ? ነግራችኋታል በካሽ እንደሆነ የምትሠሩት" አለች ፊቷን ወደልጆቹ መልሳ። ንግግሯ ፈጣንና ቃላቶቿ የተደራረቡ ናቸው። በዚያ ላይ ወፍራም ከንፈሯን በየደቂቃው ትመጠዋለች። ሁሉንም ቃኘኋቸው። የሚጠይቁኝ ጥያቄዎች ከኔ ውጭ የሆነ እና እኔን የማይመለከተኝ ግን እነሱ እንደማላውቅ እርግጠኛ የሆኑበትን እና መረጃ ሊሠጡኝ ስለሆነ እኔም እንደማላውቅ ሆኜ እንደአዲስ ከነሡ መሥማት ጀመርኩ። "ቤተሠብ ጋር ናቸሁ? ወይስ?" ንግግሬን አልጨረስኩም "ሼልተር ነን" ይሄ ክረምት ይለፍላችሁ ። ተረጋጉ። ከዚያ የሚሆነው ይሆናል። "የሚገርመው አዲስም ቀድሞም የመጣ ያው ነው። እንዴት አንዱ ከአንዱ አይሻልም?" ጥያቄውን ወደጓደኞቹ በመዞር ተናገረ። "ኧረ ቀልደኞች ናቸው በሶስት ወራቸው እቧ ይላሉ። የሚገርምሽ አመት ከሶስት ወር ሆኖኛል። ነግሬያቸዋለሁ አላመኑኝም። እስኪ ባክሽ ለኔም ፈልጊልኝ በናትሽ ምንም ይሁን እሰራለሁ።ስራ የለም።" መተንፈስ ፈልጌ አቃተኝ። እንደማንተዋወቅ እያወኩኝ ፣የማይመለከተኝን አቤቱታ ሠምቼ ፣ የልጆቹን ግራ መጋባት፣ ንቀት፣ አውቃለሁ ባይነት አይቼ ግን ደግሞ እንዴትና በምን መንገድ እንደምለያቸው፣ ወይ ምን ተስፋ እንደምሰጣቸው ጨንቆኝ ስራ መድረስ ካለብኝ አስራአምስት ደቂቃ ዘግይቼ አብሬያቸው ቆምኳ። አለችኝ። Nov 15/2023
test