ዶግማና ቀኖና...ቀሲስ ዶክተር መብራህቱ ኪሮስ ገብሩ
Edited by : addiskignit@gmail.com -1/27/2023
ዶግማና ቀኖና ሰሞኑን “ዶግማ እንጂ የማይለወጠው፣ ቀኖና ሊሻሻልና ሊቀየር ይችላል” የሚል ነገር በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምተናል፡፡ አባባሉ ከፊል እውነታ አለው፡፡ የተነገረው ግን፣ ለሕገ ወጡና ለተወገዘው ሢመት ሽፋን ለመስጠት ስለሆነ በዚህ አጋጣሚ ከላይ ባለው ርእስ ትንሽ ነገር ለማለት እሞክራለሁ፡፡ ዶግማ ምንድን ነው? ቀኖናስ? ዶግማ በዓለም አቀፍ ጉባኤያት (ecumenical councils) የጸደቀ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን ከአበው የተቀበለችውን እምነት የምትገልጥባቸው አስተምህሮዎች ደግሞ doctrines ይባላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው” ይህ ዶግማ ነው፤ “ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ናት” ይህም እንደዚሁ፡፡ የክርስቶስን አምላክነት ለማይቀበሉ አርዮሳውያን፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያን አስተምህሮ (doctrine) ተከትላ መልስ ሰጥታለች፤ ስትሰጥም ትኖራለች፡፡ ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ (Theotokos) ብለው ለመቀበል ለሚቸገሩ ንስጥሮሳውያን ደግሞ፣ እንዴት ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም “ወላዲተ አምላክ” እንደምትባል የምንገልጥበት ወይም የምናስተምርበት ዶክትሪን፣ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ እነዚህ አስተምህሮዎች በዓለም አቀፍ ጉባኤያት የተወሰኑ ሲሆን፣ ውሳኔያቱን ከተጨማሪ ጉዳዮች ጋር የቤተ ክርስቲያን አበው በቀኖናት (canons) አጽድቀዋቸዋል፡፡ ለምሳሌ እንደ አውሮጳውያኑ አቆጣጠር በ325 ዓመተ እግዚእ (AD) የተጠራው ጉባኤ ኒቅያ 20 ቀኖናት አሉት፡፡ እነዚህንና ሌሎቹን ዓለም አቀፋዊና ብሔራዊ ውሳኔያት፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ከርስቲያን Holy Canons (ቅዱሳት ቀኖናት) በማለት ትጠራቸዋለች፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳት ቀኖናት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በዓለም አቀፍ ጉባኤያተ አበው የጸደቁና የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ የሚያንጸባርቁ (ከዶግማዋ ጋር የሚስማሙ እንጂ፣ የማይጋጩ) ናቸው፡፡ “ቀኖናት ይሻሻላሉ/ ይለወጣሉ?” የሚል ጥያቄ ቢነሣ፣ መልሱ “እንደ ቀኖናው አይነት ይወሰናል፤ የሚለወጥና የማይለወጥ አለ” ነው፡፡ ለምሳሌ የክርስቶስን የባህርይ አምላክነት ወይም የመለኮትና ትስብእትን ተዋሕዶ አስመልክቶ ቅዱሳን አባቶቻችን የወሰኗቸው ቀኖናት Dogmatic Canons ስለሆኑ ማንም ተነሥቶ ሊለውጣቸው አይችልም፡፡ Practical የሆኑ ጉዳዮችን በሚመለከቱ ቀኖናት ላይ ግን፣ በሐዋርያት መናብርት የተሾሙ አበው ወይም የእነርሱ ተከታዮች (ተላውያነ አበው) የሆኑ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባዔ (ቅዱስ ሲኖዶስ) ማሻሻያ ማድረግ ይችላል፡፡ ማሻሻያ ከተደረገባቸው practical canons መካከል አንዱን ልጥቀስ፡፡ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፡- ቅስና መሾም የሚገባው ሰው 30 ዓመት የሞላው እነደሆነና ኤጲስቆጶስ ደግሞ በ50 ዓመቱ መሾም እንዳለበት የሚደነግግ ቀኖና ነበር፡፡ በሂደት ግን ቤተ ክርስቲያን ተምረውና በቅተው ለተገኙ ልጆቿ 30 ወይም 50 ዓመት ባይሞላቸውም የቅስና እና ጵጵስና መዓርግ ሰጥታለች፡፡ ወገኖች! Apostolic Succession (ሐዋርያዊ ሰንሰለትን) በመጠበቅ ተወዳዳሪ የሌላት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት በተቀደሰው ትውፊት (Holy Tradition) አማካኝነት ቅዱሳት መጻሕፍትንና ከእነርሱ የሚመነጨውን ርቱዕ (የቀና) አስተምህሮ ያስረከበችን፣ ማንም የመሰለውን መላምት እያመጣ ከቀጥተኛው (ኦርቶዶክሳዊ) መንገድ እንዳይወጣ አጥር ሆነው የሚጠብቁ Holy Canons (ቅዱሳት ቀኖናት) ስላሏት ነው፡፡ ይህን ለመረዳት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የአምልኮ ውበት እና ሥርዓት፣ Protestantism ውስጥ ካለው ቀውስ (chaos/anarchy) ጋር በማነጻጸር መረዳት ይቻላል፡፡ “ቀኖና የሚሻሻል ነገር ነው” በሚል ጥራዝ ነጠቅ አነጋገር፣ በዘመናት ተፈትኖ ያለፈውንና በምድር ላይ ሆነን ሰማያዊ ሐሴትን እንድንለማመድ የሚያደርገንን ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓተ አምልኮ ሸርሽረን ወደ ፕሮቴስታንታዊ ሥርዓት አልበኝነት እንዳንገባ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ የአኰቴተ ቁርባን ጸሐፊው እና የቀድሞው የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ዲን ቀሲስ ዶክተር መብራህቱ ኪሮስ ገብሩ
test