ዓርብ፣ቅዳሜና እሁድ - /ሶስና አሸናፊ/
Edited by : sosina ashenafi -12/25/2025

የፎቶ ባለሙያ አይደለሁም። ካሜራዬን በእጄ አንጠልጥዬ ስለምዞር "አለማየሁ ፎቶ" ይሉኛል ።  በናይት ክለቦች የሳምንቱ መጨረሻ ዓርብ፣ ቅዳሜና እሁድ አበሾች ከሚገኙበት አልጠፋም። አየሩ ቀዝቅዟል። በጠባቡ ናይት ክለብ የተገኘው ሰው ገና መድረሱን ለማወጅ ይመሥል ጃኬቱን ለመስቀል ይተራመሣል። ቀኑ የፈረንጆች ገና ዋዜማ ነው ። 

 ማሂ የምወደውን ቀይ ከፋይ ቀሚስ እንደለበሰች በቀሚሷ ላይ የውስጥ ሱሪዎን በሁለቱም እጆቿ ከፍ እያደረገች ስታልፍ ያ ሁሉ ለሰማይ ለምድር የከበደ ትልልቅ ሰው ምራቁን ሲውጥና አይኑን ጭኗ ላይ ሲያንከባልል በአይኔ አይቻለሁ እና ፈራሁ። ሆን ብላ ሳይሆን ሳታስብ በተዘበራረቀ ነገር ውስጥ እንዳለች ሳይታወቅ አንዳንድ ነገሮች አፈትልከው ይወጡባታል። ያም ሆኖ ድንበሯን ጠባቂ ነች። አጭር ቀሚስ ያምርባታል። ጭኗን እግዜር ተጠቦባታል። ከጭኗ እስከ ጉልበቷ ያለው ውበት ያስመንናል። እኔ ደግሞ እወዳታለሁ ብዬ በምሳሳላት ልክ ለማንም ተናግሬ አላውቅም።ውስጧ የውበት አማልክት ሰፍረውባታል። ንቁ ነች። የሰው ነገር ግድ ይላታል። በዚያ ላይ ተለማማጭ። በዚያ ላይ ቅን። እኔን ግን ታሳዝነኛለች። ካለቦታዋ የዋለች ይመሥለኛል።ከቀሚሷ ስር የሚደንሰው ብቸኝነቷን እና ኩሏ ላይ የተንጠለጠለ ብሶቷን ሳይ ወንድነቴ ይከዳኛል። አጠገቧ በመገኘቴ ከሁሉም የተከላከልኳት ይመሥለኛል። ይህንን ደግሞ ለማንም ማሳየት አትፈልግም። ከውበቷ ባሻገር እኔንም አስሮ ያስቀረኝ ይሄው ይመሥለኛል።በሄደችበት እከተላታለሁ ። 

እሷም "አሌክስ እንዳትቀር " ትለኛለች ስንሰነባበት በሁለት እጆቿ እቅፍ ታደርገኛለች። ጨምድጄ ለተወሰነ ደቂቃ ደረቴ ውስጥ እሸጉጣታለሁ። ደግሞ ትናፍቀኛለች። በምንገናኝበት ቦታ የታዘበችውን እያንዳንዱን ነገር እየቆጠረች "ቅር እንዳይልህ ነገ ሌላ ቀን ነው እንዳትቀር ዋ!" ትለኛለች ደጋግማ። 

በተለይ ያንን የናይት ክለቡን ባለቤት ማየት ሲያስጠላኝ ትረዳኛለች። በእኔና በእሷ መሀከል ሊገባ ያምረዋል። አንዳንዴ መፈጠርን የሚያስጠላ ባህሪውን ያወጣዋል። ከአርባ ሀምሳ አመት በላይ መኖሩን ይነግረኛል። ደግሞ ደጋግሞ ይተርክልኛል ። ለኔ ግን ከንቱ ነው። በክለቡ ውስጥ እሷን ተቆጣጣሪ አድርጎ ከቀጠራት ሶስት አመት አልፏል ብላኛለች። ሲያሻው እሷን ያማልኛል፣ሲያሻው የቀኑ እንግዳው ያደርገኛል። ተደጋጋሚ ቀኖች ልገልፀው እና ላስታውሰው የማልፈልገውን ነገር አድርጎኝ ያውቃል። ግን ማሂ አለች። ማንን ወዶ ማንን እንደሚጠላ አይታወቅም።ብቻ እሷ እንዳይከፋኝ በዛ በሚያባብል አይኗ ትዳብሰኛለች። እኔና ማሂ የተዋወቅነው ቤተክርስቲያን ደጃፍ ነው። ጉዳዬ አላለቀም ስላት "እግዛብሔር ያውቃል እኔም እንዳንተው ጠባቂ ነኝ""አለችኝ። ዝርዝር ነገር አላወራንም። ከምትሰራበት እንድመጣ ጋበዘችኝ ሄድኩ ተገናኘን።

አንዳንዴ ካሜራዬን እንደያዝኩ ጭልጥ ያለ ሀዘን ውስጥ እገባለሁ። የሀዘኔ መነሻ በሰው ሀገር መገኘቴ ፣ የጉዳዬ መጓተት ይሁን እሷን ድንገት መውደዴ እንጃ! ሁሉ ነገር አሳስቦኛል።  በዚያ ላይ የማየው የሰዎች የክፋት ጥግ ይረብሸኛል። ሳንተዋወቅ እንራኮታለን። ሳንግባባ በወሬ እንለያያለን።መራኮታችን ደግሞ ሰንዝር አላራመደንም። ላንጨርሰው ያላለቀ ነገር መቀባበል ያምረናል። እራሳችንን መሾም እና እኔ ነኝ ተገቢ ማለት እናበዛለን እላለሁ ለራሴ ብቻዬን ስሆን፤ ከሀገር ወጥተን መቅረታችን አየተዋወቅን አለመረዳዳታችንን ሳውቅ ደግሞ ሀዘን ውስጥ እወድቃለሁ። ግን ብቻዬን ነኝ።ብቸኝነቴ ይፈታተነኛል። እሷ ብቻ የምትረዳኝ ይመሥለኛል። ሀዘኔን አዳምጣ "አሌክስ እራት እኔ ጋ አለ"ትለኛለች። በእረፍት ሰአቷ ራት አብረን እንበላለን እንጂ ስለሷም ሆነ ስለኔ አናወራም ። እራት አብረን መብላታችን ዋጋው ትልቅ ነው። ብቻ "ለምን ሌላ ቦታ ስራ አትቀይሪም?" አላታለሁ።

"ቤቱን እወደዋለሁ ግርግር የለውም" ትለኛለች።

"መሥራትሽ ላልቀረ ተጠቀሚ ብዬ ምክንያት ልደረድርላት ስጀምር አታስጨርሰኝም።


እጅዋን አፌ ላይ ትከድነዋለች።

ይገባኛል ባለቤቱ እንዳይሰማ ነው።

እኔ ግን በጣም እበሳጫለሁ። 


ባለቤቱንም ያለ ገደብ እጠላዋለሁ። ያቅፋታል። ዛሬ እጁን ወገቧ ላይ ዳብሶ ሲያስቀምጥ አይቻለሁ። እሱም አይቶኛል።

"አሌክስ አንሳን" አለች ከተሠበሠቡት ጓደኛማቾች መሀል ገብታ። ፎቶ መነሳት ትውደድ ወይ ግርግር መፍጠሪያዋ አልያ እኔን ስራ ለማሰራት እንጃ! ብቻ ግን ተሰብስቦ መነሳት ትወዳለች። 

አሱ ወደጡቷ ቀርቦ እግሩን ወደ ጭኗ አስጠግቶ ፎቶውን ተነሳ ። ይህንን እንደሌላው ጊዜ ማሳየት አልፈለኩም። ፎቶአቸውን ስሰጣቸው አስርም አምስትም ዶላር ይሰጡኛል። 

"ና አሌክስ ሰልፊ እንነሳለን አብረን ሁላችን" አለች


አጠገቧ ስደርስ ሀዘን በጠበሰው አይኗ እባበለችኝ። ከዚህ በፊት ሰልፊ እንነሳ ብላኝ አታውቅም። የጨነቃት ትመሥላለች። 

ሳላስበው እኔእና እሷ ብቻ እንዳለን ቆጥሬ አቅፌያት እየተሽከረከርኩ በዘዴ ከጉሩፑ እንደመራቅ እያልኩኝ ደጋግሜ አነሳሁ። ወገቤ ላይ ያረፈው እጇ እንደሞቀኝ ሁሉ ትከሻዋን ያቀፈው እጄም አልቦታል። ካሜራው ውስጥ ያለው መልኳ አሳዘነኝ ማዲያት አውጥታለች እና ዞር ብዬ አይኗን ስፈልገው ከንፈሯ በድንጋጤ ይንቀጠቀጣል። አላስቻለኝም በሁሉም ፊት ሳምኳት። 

ካደረኩት በኋላ ግን የምገባበት ጠፋኝ። ብዙ ነገር እንዳበላሸሁባት የተረዳሁት ሁሉም አይናቸውን ሲያፈጡብኝ ነው። ደንግጫለሁ። ግን ደግሞ ከዚያ ሁሉ አፍጣጭ እና ደፋር ፊት በማድረጌም ደስታ ተሰምቶኛል። 

እሷ ግን የተሠማትን ወዲያው አልገለፀችም። ከቆይታ በኋላ ሚስጥር እንደምትነግረኝ በሚርገበገብ ድምፅ ወደጆሮዬ ተጠግታ

" አሌክስዬ ! ማምለጫዬ ስልህ? ለምን አደረከው? ሁለት ልጆች እናትና ባለትዳር ነኝ ኦኮ" ስትለኝ ለማሰቢያ ጊዜ ሳይኖረኝ ድንጋጤ ውስጥ ወደኩ። እጇን ከወገቤ ላይ አንስቼ ወደሰውነቷ እየመለስኩ እንባዋን ሳልጠርግላት ሰውነቴን ማዘዝ እያቃተኝ በሩን ከፍቼ ወጣሁ።

test