
ጌትነት እንየውን ያህል ጠቢብ ከስንት ዓመታት ብሔራዊ ዝንጋታ በኋላ አበርክቶውን በሚመጥን ደረጃ መከበርና መሸለሙን በስደት ከምኖርበት ሀገረ ካናዳ ሆኜ ስሰማ በእጅጉ ደስ አለኝ። ለዚህም የተስፋ ኢንተርፕራዙ ተፈራ ወርቁ የአንበሳው ድርሻ እንደሚወስድ ቴዲ ተክለአረጋይ ነገረን ተባረክ ብያለሁ ተፌ።
ጌትነት እንየው በ1970 ዎቹ እና 80ዎቹ የኢትዮዽያ ቴሌቪዥንን ይመለከት ለነበረ ለማንኛውም ኢትዮዽያዊ የታወቀ ስም ነው።በ 1985/6/7/8/9/ እና 90 ዎቹ የጌትነት ወርቃማ የትወና የማዘጋጀት እና የመፃፍ ወራት ነበሩ። በቴአትር ክበብ ነፃ መግቢያ ትኬት ካየሁአቸው መሀከል
የሻምበል ፈቃደ ዮሃንስ ድርሰት እና የጌትነት ዝግጅት እና መሪ ትወና የነበረው እርጉም ሐዋርያ
የጋሽ ፀጋዬ የሼክስፒር ትርጉምና የማንያዘዋል እንደሻው ዝግጅት ሐምሌት
ለመቼውም ጌትሽን የማስታውስባቸው ሥራዎች ናቸው።
ጌትነት ፀሐፈ ተውኔት አዘጋጅና ተዋናይም ብቻ አይደለም ጥንቅቅ ያለ ገጣሚም ነው።አሪፍ የአጫጭር ልብወለዶች ፀሃፊም ነው በድሮው የብሔራዊ ቴአትር አመታዊ መጽሔት ከሙያችን ላይ ይወጡ የነበሩ ግጥሞች እውቀትን ፍለጋን እስኪያሳትም ድረስ አድነን የምናነባቸው ነበሩ።በ90ዎቹ በሰለፍ የታየው ውበትን ፍለጋ ተውኔት የጌትነት ብዕር ለፈለገው ዘውግ የሚገዛ መሆኑን ያረጋገጥንበት ነው።
አባ ኮስትር በላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን በታየ ጊዜ ባለቀለም ቴሌቪዥን የመጣበት ጊዜ ነበርና ብዙው የሰፈራችን ወጣት ወደ ቀበሌ ክበብ ሄዶ ነበር የሚያየው እና እኔም የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊ ጄነራል ዊንግት አካባቢ ወደ ኮልፌ መንገድ ላይ ከነበረው የከፍተኛ 25 ቀበሌ 02 የወጣቶች መዝናኝ ሄጄ ነው የጌትነትን አባ ኮስትር ያየሁት ታዲያ ያችን ጠባብ የመዝናኛ ክበብ የሚመራት የጀግናው በላይ ዘለቀ ወይም አባ ኮስትር የልጅ ልጅ መሆኑ ትርኢቱን አይረሴ ያደርገዋል። የአካባቢው ሰው ቹቹ እያለ የሚጠራው እኩዮቹ ነብሮ የሚሉት ተክለማሪያም ባህሩ ከበላይ ዘለቀ ልጆች አንዱ የነበረው የባህሩ ልጅ ነው። አባቱ በልጅነቱ ቢሞትም እናቱ አባይነሽ በድህነት ጥጥ ፈትላ እንጀራ ጋግራ ነው ያሳደገችው።
ጌትነት እንየው አባ ኮስትርን ሲጫወት እኔ እናቴ አንዴ በላይ ብላኛለች ሌላ ማዕረግ አልፈልግም ሲል በተክለማሪያም ፊት ደማቅ ብርሃን ነበር የፈነጠቀው።
ጌትነት እንየውን ከዚያ በኋላ የማየት የማግኘት የማናገር ጉጉት ውስጤ ተፈጠረ።
ያ ጊዜ አልፎ ወያኔ አገር ከወረሰ በኋላ እኔም ወደኪነት አዘነበልኩ በሰፈራችን ደብር ዼጥሮስ ወ ዻውሎስ መድረክ የተጀመረ የድራማ ሙከራ አድጎ ፒ ኤንድ ፒ ወይም ዼጥሮስ ወ ዻውሎስ የተሰኘ ክበብ አቋቋምን ከአዲስ አበባ ባህል ቢሮም ፈቃድ አግኝተን ከቀዳሚዎቹ ከነ አፍለኛው እኩል ተውኔት መስራት ጀመርን አጋጣሚ አንዷ አባላችን ያመጣችው የተውኔት ፅሁፍ እጃችን ላይ ገባ ማርታ እና ሐና የተሰኘ በደረጀ ኃይለሥላሴ የተፃፈ ባለ አንድ ገቢር ተውኔት ነበር በዚያን ወቅት ኮልፌ እፎይታ ገበያ አጠገብ እየመጡ ተውኔት በግላቸው ከሚያሰለጥኑንና ከሚያበረታቱን ፕሮፌሽናል የቴአትር ሰዎች መሀከል የማዘጋጃ ቤቱ ተዋናይና አዘጋጅ ከበደ ደገፉ እንዲሁም ድሮ በዼጥሮስ ዘኬ አድጌአለሁ እያለ የሚያስቀን በኃይሉ መንገሻ አንዱ ነበር።
ከበደ ደገፉ ቤቱ አስኮ ስለነበር በየሳምንቱ አንድ ቀን አንዳንዴም ከዚያ በላይ እየመጣ ያሰለጥነናል አተዋወን መድረክ አያያዝ ብሎኪንግ የድምፅ አወጣጥ ወዘተ። እና የደረጀን ተውኔት እንዳገኘን ስንነግረው በክበቡ ውስጥ ያሉትን ልጆች ካስት አድርጎ ተውኔቱን ግሩም አድርጎ አዘጋጀው።
ተውኔቱ ማርታ በምትባል ተዋናይት እና መተወኗን በሚቃወም ነጋዴ ባሏ መሀከል የሚፈጠር ግጭት ላይ የተመሰረተ ነው እሷ ልተውን ስትል እሱ አርፈሽ ተቀመጭ ወይም እኔ ሱቅ እከፍትልሻለሁ ባይ ነው። በኋላ ወደ ጡዘቱ ሲቃረብ ለረዥም ጊዜ ተደብቃ ያጠናችው ተውኔት ለህዝብ የሚከፈትበት ቀን ይደርሳል እና ቧሏን አታላ እና እንደማትሄድ ቃል ገብታ እሱ ሲሄድ ወደ ቴአትር መክፈቻው ትሄዳለች የመድረክ ስሟ ሃና ነው መድረኩ ላየ የመሳሳም ትእይንት አለው እና ፍቅረኛዋ ሊስማት ሲል ከህዝብ መሀል እንዳትስማት ሲል ባሏ ሽጉጥ ደግኖ ይነሳል።
ይህን ልብ አንጠልጣይና መሳጭ ታሪክ የሚተውኑት የክበባችን ልጆች ማርታን ሰርካለም ተስፋዬ
ባሏን ታዬን ቶማስ ተስፋዬ
አዘጋጁን ሃይሉ ስዩም
ፍቅረኛዋን አሀዱ ነበሩ ሌሎችም እንደየሁኔታው አነስተኛ ሮል ተሰጥቷቸዋል።
ይህን ተውኔት ይዘን በየቦታው አሳይተናል ደብረዘይት ናዝሬት አዲስ አበባ እዚያ አዳራሻችን ኮልፌ አጠና ተራ ከፍተኛ 25 ቀበሌ 08 አዳራሽ ።
በወር አንዴ የሥላሴ እለት አብሮን የሚያሳልፈው በኃይሉ መንገሻ /ነፍስ ይማርና/ ለምን ብሔራዊ አታስገመግሙትም የአዘቦት ቀን ቲአትር ከውጪ ማሳየት ስለተፈቀደ ጥሩ ይሆናል አለን። እንደተባለው በደብዳቤ ፕሮዳክሽኑ እንዲገመገምልን ለቴአትር ክፍል ጠየቅን እና አስፈላጊውን አሟልተን ተገመገመ እና አልፏል ተባልን። ለመድረክ ከመብቃቱ በፊት ግን ዋናው አዘጋጅ እና ደራሲው መምጣት አለበት ተባለ። በእኛ አጠራር ለከቤ ወይም ከበደ ደገፋ ነገርነው እኔ አልሄድም ቶማስ ረዳቴ ስለሆነ እሱ ይነጋገር አለ።ሆኖም በክበብ አባላት መሀክል ቶማስ ሆኖ የአዘጋጁ ክፍያ በሙሉ ወደሱ ይሂድ የሚለው ሊያስማማ ስላልቻለ የብሔራዊ ሰዎች ጌትነት እንየውን አምጥተው የተወሰነ ማስተካከያ አድርጎ ለቤቱ መድርክ በሚመች መንገድ ሪ ዳይሬክት እንዲያደርግ መደቡት እሱም በደስታ አደረገ በተለይ መሪዋን ተዋናይት ሰርካለምን ማርታንና ሃናን ሆና ስትጫወት ሲያያት በግሬሳ በመድረክ በቃቷ ተደሰተና በሳምንት ሁሌቴ እየተገናኘን እንስራ ብሎ ቀን ቆረጠ ሰርካለም ግን በተባለችበት ቀን አልመጣ አለች ብትመጣም እያረፈደች የጌትነት የማዘጋጅት ጉጉት ውሃ ደፋችበት እስካሁን በሚገርመኝ ሁኔታ ሙላለም ታደሰ እንድትሆን ብሎ ይዟት ሲመጣ ሙላለም ሙሉ ቃለ ተውኔቱን በቃሏ ይዛው ነበር ። እና ያ ተውኔት ሊከፈት ሲል ጌትነት እኔ አዘጋጅ አልባልም አዘጋጁ ከበደ ነው እኔ እንዲያው ለመድረኩ ኣስማማት ነው ሲል እራሱን ከክፍያ አወጣ።ይህ የጌትነት ለገንዘብ ለዝና ያለውን ጤነኛ አስተያየት እና ለሙያው ያለውን ክብር ያረጋገጥኩበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነው።
ያን የመሰለ ቴአትር በየሳምንቱ ሐሙስ በብሔራዊ ቴአትር መታየት ከጀመረ በኋላ እንዲቋረጥ ሆነ ። ለመቋረጡ ምክንያት የሆነው የደራሲውን ክፍያ በክበባችን ላቀረብነው ለሟቹ ደራሲ ህጋዊ ወራሽ የቴአትር ቤቱ ቴአትር ክፍል ሃላፊዎች እነ ፈቃዱ ፈዬ አልከፍልም በማለታቸው እኔ ጉዳዩን ጋዜጣ ላይ ለመጻፍ ተገደድኩ አዲስ ዘመን የፃፍኩትን ባህል አምድ ላይ እንዲያወጣልኝ ያኔ የባህል አምድ ለሚያዘጋጀው ወዳጄ አብረሃም ረታ ሰጠሁት ጥቂት ቀን አቆይቶ ከብሔራዊ ወዳጆቼ ጋር ታጣላኛልህ ብሎ አላወጣ ሲለኝ ያኔ እንደአሸን ከፈሉት ታብሎይዶች ማከሰኞ ቀን ለሚወጣው ኤሪስ የተባለ ጋዜጣ ሰጠሁት በትልቁ አትሞ አወጣው በሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ሀገር ሰላም ብለን ብንሄድ ማርታ እና ሐና ቴአትር ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል ተብሎ መግቢያው ላይ ማስታወቂያ ተለጥፎ ጠበቀን።
ይህ ከሆን ከጥቂት አመታት በኋላ በኢትዮዽያ ቤተሰብ መምሪያ ማኀበር የኮልፌ ቅርንጫፍ ከሟቹ ደራሲና ተዋናይ ሰለሞን አለሙ አብዬ ዘርጋው ጋር ሆነን እሱ የቴአትር እኔ ኢትዮ ራዕይ የተባለ ክበብ አቋቋምን የ6 ወር ስልጠና ከሰጠሁ በኋላ በስልጠናው ፍፃሜ የምረቃ ዝግጅት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዘጋጅተን ጋዜጣ አሳተምን ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና አዘጋጅነት የሰራኋት ጋዜጣ ናት ። ለኪነ ጥበብ አምድም በእንግድነት የመረጥኩት ጌትነት እንየው ነበር በቀጥታ ብሔራዊ ቴአትር ሄጄ ያለምንም ቢሮክራሲ የህይወት ታሪኩን ከ ሀ እስከ ፐ ተረከልኝ።
ጌትሽ ትናንትም ዛሬም ኢንቴግሪቲውን የጠበቀ ለኪነት ራሱን የሰጠ ታላላቆቹን አክባሪ ታናናሾቹን መካሪ ነው። እድሜና ጤና ሰጥቶት ብዙ እንዲፅፍልን በተለይ ግለ ታሪኩን እንዲፅፍልን ምኞቴ ነው።