ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
Edited by : addiskignit@gmail.com -3/7/2023
ማክሰኞ የካቲት 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ዘርፍ ከሚጠቀሡት አንጋፋ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች መካከል ዋነኛ የሆኑት የሥነ ጽሑፍ መምህርና ሐያሲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ‹‹የሥነ ጽሑፍ መሰረታውያን›› እና ‹‹ከበዓሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ›› የሚሉ ለሥነ ጽሑፍ ትምህርት አጋዥ መጻሕፍትን ጨምሮ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያሳተሙት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን፤ በፍቅር እስከመቃብር መጽሐፍ ዙሪያ የተለያዩ ጥልቅ ጥናቶችን ማድረጋቸው ይነገራል። ሰሞኑንም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሰውመሆን ፊልሞች ጋር በመተባበር ለሚሰራው "ፍቅር እስከ መቃብር " ባለ 48 ክፍል የቴሌቪዥን ድራማ ጥናት እንዲያቀርቡ ከተመረጡት ምሁሮች መካከልም አንዱ ነበሩ። ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሥነጽሑፍን ያስተማሩና የአማርኛ ሥነጽሑፍ ታሪክን እና ቴክኒክን ያጠኑ ያስተማሩ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ጽሑፍ መምህርነት እና አማካሪነት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን እስከትናንት ለሊት ድረስ በጤና ሲጽፉ አምሽተው ለሊት ላይ በድንገት ማረፉቸውን አዲስ ማለዳ ከረዳት ፕሮፌሰሩ የቅርብ የሙያ አጋሮች ለማወቅ ችላለች።
test