
"የሥነ ጽሑፍ ሣሎንን ከተቀላቀልኩ ገና 11ኛ ወሬ ነው ... ዓመት አልሞላኝም ... ገና አንድ ወር ይቀረኛል ..." ብዬ ዳሰሳዬን ብጀምር ‹ቀደም ብለህ ይሄንን ብታሳውቀን ኖሮ ላንተ ሲባል ክብረ-በዓሉን ለአንድ ወር እናዘገየዋለን› የሚል ስላቅ እንደምትሸጉጡልኝ አውቃለሁ።
የሥነ ጽሑፍ ሣሎናችን ለአንድ ዓመት ሙሉ ካደረጋቸው ውይይቶች፣ ገጠመኞች፣ ክንውኖች አንኳር አንኳር የሚባሉትን በአጭሩ እንደሚከተለው እዳስሳለሁ።
ሰኞ ሰኞ ባለው በግጥም ቀናችን የዳዊት ጸጋዬ ግጥሞች ላይ ተወያይተን፣ የፊርማዬ ዓለሙ ግጥሞችን ኮምኩመን፣ የጋሽ ሥዩም ተፈራ የስንኝ ቋጠሮ ላይ ኂሳዊ ንባብ አቅርበን፣ የኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ብዕርን ተመልክተናል። በተጨማሪም የተለያዩ ገጣሚያንን ልዩ ልዩ ግጥሞችን በየሳምንቱ ተገባብዘናል።
ማክሰኞ ማክሰኞ በሚደረገው ደራስያንን በማስተዋወቅ ቀን የ pen international ተቋም አመሠራረትን አይተን፣ ስለመሥራቾቹ ማንነትና ምንነት ቃኝተን፣ የሠንሰለት መጽሐፍ ደራሲ ሻምበል ፈቃደ ዮሐንስን በአባሎቻችን ብዕር ጎብኝተን፣ ከአንዳንዶቻችን የዘመን ጓድ የኾነው የታገል ሰይፉን ሥራዎችና ሕይወት አውስተን፣ ስለአውግቸው ተረፈ እና እብዱ መጽሐፍ ተዝተን፣ ስለሚላን ኩንዴራ አውግተን፣ ስለፍራንዝ ካፍካና ሥራዎቹ ተቀባብለን፣ ስለ ዣን ፖል ሳርተር በመጠኑ ቀማምሰን … ድምቅምቅ ያሉ ቀናትን እና ምሽቶችን አሳልፈናል።
እንዲሁም የአፍሪካን ታሪክ ዲኮሎናይዝ ማድረግ በሚለው ሐሳብ እና ሐቀኛውንና በአፍሪካዊያን ተጽፎ የዩኔስኮን ሼልፍ ሲያሞቅ የኖረውን ሰነድ ነጻ ለማውጣት የሄደችበትን ርቀት የሚያትተው የዘይነብ በደዊ ታሪክም እንዲሁ በሣሎናችን የማክሰኞ አትሮኖስ ላይ ተሰይመው ከነበሩ ዐበይት ጉዳዮቻችን አንዱና ዋነኛው ኹነት ኾኖ አልፏል።
እሮብ እሮብ በነበረን የረጅም ልቦለድ ቀን ላይ የርብቃ ፍሥሐን ዳውተር ኦፍ ሳይለንስ ላይ ተወያይተን፣ የአዳም ረታ ሥራዎች ላይ ኂሳዊ ንባቦችን አቅርበን፣ የፍቅረ ማርቆስ ደስታ ኤትኖግራፊ ድርሰቶቹን በሚመለከት ከደራሲው ጋር በድምፅ ቅጂ ዘለግ ያለ ውይይት አድርገን ... ከቀደምት የበዓሉ ግርማን፣ የሀዲስ ዓለማየሁን፣ የዳኛቸው ወርቁን፣ የብርሃኑ ዘርይሁንን ሥራዎች … ከአሁነኞቹ የወንደሙ ገዳን፣ የስንቅነህ እሸቱን፣ የዓለማየሁ ገላጋይን እና መሰል ጻሕፍትን ሥራዎች ላይ በልዩ ልዩ መንገድ አውስተናል፣ አውግተናል፣ ተከራክረናል … ተወያይተናል። በተጨማሪም በዐማርኛ የተከታታይ ልቦለዶችን መልክ ቃኝተናል። ሦስትዮሻዊ ( trilogy ) የልቦለድ መጻሕፍት ላይ ምልከታችንን አንጸባርቀናል።
በሐሙስ የኢ-ልቦለድ ቀናችን የተስፋዬ ማሞን ከማዕበል ማዶ፣ የማልኮም ኤክስን የሕይወት ታሪክ፣ የፍቅረማርቆስን የሚሳም ተራራን፣ የነብይ መኮንን የኛ ሰው በአሜሪካን፣ በጥላሁን ገሠሠ ዙርያ ዘካሪያ መሀመድ በጻፈው መጽሐፍ ላይ እና መሰል የኢልብወለድ ሥራዎች ላይ ሄደንበታል።
የኂስ ቀናችን በኾነው በዕለተ አርብ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዕይታችንን ተቀባብለናል። ስለ ኂስ ምነነት፣ ስለ ኃያሲነት፣ የኃያሲያንን እጥረት ለመቅረፍ፣ ጥራታቸውንም ለማላቅ በዩኒቨርስቲዎቻችን ሥነ-ኂስ ላይ ብቻ ያተኮረ department መቋቋም አለበት ወይስ የለበትም? በሚል ጉዳይ ሐሳብ ተለዋውጠናል። ከደርግ በኋላ የሴንሰር መቆም ሥነጽሑፋችንን ጎድቶታል ወይስ ጠቅሞታል? በሚል ሞቅ ያለ ውይይት አድርገናል። የደራሲ ሞትና የአንባቢ ልደት የሚለውን ጥልቅ ሐሳብ ላይ … ጠንከር ያሉ የሙግት ቡጢዎችን በፍቅር ተቃምሰናል።
የአጭር ታሪኮች፣ የአጭር ልቦለዶች፣ የወጎች ሰንዱቅ ማጠንጠኛ ቴፕ በሚከፈተው በዕለተ ቅዳሜ የአንቷን ቼኾቭ ሥራዎችን፣ የምግባር ሲራጅ እየዳነ ኼደን፣ የተመስገን ገብሬ አጭር ልቦለድን፣ የትግስት ሳሙኤል፣ የአሌክስ አብርሃም፣ የታደሰ ሊበን፣ የሶስና አሸናፊ … እና መሰል ደራሲዎችን ተገባብዘናል፣ ተቀባብለናል፣ ተወያይተናል።
በተለያየ ወራት የተዘጋጀ የዙም ውይይት በአራት ዙር የቀረበ ሲኾን
1. አብዮተኞች እና ሥነጽሑፍ በሚል መነሻ ሐሳብ ጋሽ ቤልጅግ ዓሊ፣
2. ንባብ ሙሉ … መጻፍስ ሙሉ ያደርጋል በሚል ርዕስ ጋሽ ገዛኸኝ መኮንን፣
3. በሀገራችን ንባብን ለማገዝ ምን እናድርግ በሚል ጋሽ ዓለሙ ተበጀ
እንዲሁም
4. የኢትዮጵያዊ ዘመናዊ ልቦለድና አብዮት በተሰኘ ርዕሰ ጉዳይ ላይ - ጋሽ ቢኒያም አቡራ
አማካይነት መነሻ ሐሳብ ቀርቦ በዙም መተግበሪያ ተገናኝተን ሰፋ ያለ ውይይት አካሄደናል።
የልደት ቀን አከባበር፣ የጋብቻ ክብረ-በዓል፣ ሀገር አቀፍ ክብረ በዓላት፣ ዓለምአቀፍ ክብረበዓላት፣ ታላላቅ ኤቨንት እና መሰል መርሐግብሮች የመልካም ምኞት በመግለጽ ቤተሰባዊነትን ያደረጀንበት አጋጣሚዎች ናቸው። በዓላቱን የምናከብርበትን መንገድ ለአባላቱ በመንገር ይበልጥ የተዋወቅንበት ሣሎን ነው። በተጨማሪም በዓላቱን ተገን በማድረግም ሥነጽፋዊ ሥራዎችን የምናወሳበት መኾኑን ልብ ይሏል። ለምሳሌ በላብ አደሮች ቀን እንደ ቱሉ ፎርሳ ያሉ ጽሑፎችን፣ በፋሲካ በዓል ወቅት ገጸክርስቶስ ገጸባሕርያትን፣ በእስልምና በዓላት ሰሞን እስላማዊ ሥነጽሑፍን መተዘታችን ለአብነት የሚጠቀሱ ክንውኖቻችን ናቸው።
ከሀገር ውስጥ እነ ፍቅረዐዲስ፣ አስቻለው ፈጠነ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ሰይፉ ዮሐንስ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ጂጂ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ሙላቱ አስታጥቄን … ከውጭ እንደ ያኒ፣ ትራምፒስትና የጃዝ ሙዚቀኛውን ሉዊስ አርምስትሮንግ፣ የፈረንሳይቷ ኤዲት ፒአፍን፣ ሬይ ቻርለስን እና መሰል ሙዚቀኞችን እየተገባበዝን ለአንድ ዓመት ዘልቀናል።
እንደ የአልጋ መውረጃ፣ እንደ አምበር ጭቃ፣ እንደ ፈድለ-ተቃርኗዊ ያሉ ያልገቡን ቃላት፣ አባባሎች፣ አገላለፆችን የምንለዋወጥበት፣ የምናስተረጉምበት፣ መጠነኛ ጨዋታ የምንፈጥርበት ሣሎን ኾኖ ለአንድ ዓመት ዘልቋል።
እንደ ሀጂ ሙፍቲ ዑመር ኢድሪስ ያሉ፣ እንደ የምወድሽ በቀለ ያሉ፣ እንደ ነብይ መኮንን ያሉ ሰዎችን በሕይወት ስናጣ ኀዘናችንን፣ ትዝታችንን፣ ፍቅራችንን በጠቅላላው ስሜታችንን የምናንጸባርቅበት ልቅሶ መድረሻ ድንኳናችን ነው።
የታላላቅ ከያኔያንን የልደት ቀን ምክንያት በማድረግም ስለሕይወታቸውና ሥራዎቻቸው እናወጋለን። ለአብነትም የጂጂን ልደት በማስመልከት ግጥሞቿ ላይ ውይይት ማድረጋችን አንዱ ማሳያ ነው።
አንዳንዴ ደግሞ የዝምታ ክብረበዓል እናከብራለን። ቀኑና ወሩ ሳይታወቅ የሚመጣ የዘምታ ክብረ በዓል አለን። አንዳንዴ የዝምታው ክብረ-በዓል ይረዝማል - ሲለን ደግሞ እናሳጥረዋለን።
እንደ ዓይናለም ያሉ የሚያሳዝኑ ውብ ሰዎች ደግሞ አሉ፤ "የስደት ዓለም ብዕሬን አድርቆታል" ብሎ በኀዘን የተሰናበቱን። በእንደዚህ ያለ ምክንያት ድጋሚ የምናጣው ሌላ ሰው እንደማይኖረን ተስፋ እናደርጋለን።
ደሞ ደሞ በእንቅልፍ ሰዓት ተደውሎ የረብሻ ቁርስ ቀርቦልንም ያውቃል። አንዳንዴም የተሳሳተ ሰው ወደ ኅብረቱ አስገብተን የቀደመ ፍቅር ቀስቅሰናል። በጥበብና በትዕግስትም ነገሩን ቋጭተናል። የጋሽ አበራ ለማ ሞገደኛው ነውጤ፣ የአውግቸው ተረፈ እያስመዘገብኩ ነው እና መሰል ትረካዎችን ተገባብዘናል።
እንዲህ እንዲያ እያልን ለአንደኛው ዓመታችን በቅተናል። ሁለት … ሦስት …. አምስት … ዐሥር … ሃያ … እያልን ለሃያ አምስት ዓመት ያዝልቀን! … ከ25 ዓመት በላይ ጥሩ አይደለም! 🤗
አመሰግናለሁ!
ቢኒያም አቡራ
ጥቅምት 23 / 2013