ለአንድ ሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል? -ሊዩ ቶልስቶይ እንደፃፈሙ ገዛኸኝ መኮንን አሣጥሮ እንደተረጎመው
Edited by : addiskignit@gmail.com -12/13/2022
ገበሬው ፓሆም ባለቤቱ ከከተማ ልትጠይቃቸው ከመጣች እህቷ ጋር ስታወራ ጀሮውን ቀስሮ ያዳምጣል፡፡ የሚስቱ እህት ስለ ከተማ ህይወት ምቾት ትንደቀደቃለች፡፡ ፓሆምም ማን ከማን ያንሳል በሚል እንዳቅሚቲ በተራው ጉራ ለመቸርቸር ሞከረ፡፡ “ከመሬት ማነስ በቀር እኛም የቸገረን ነገር የለም፡፡ መሬት እንደልቤ እግኝቼ ቢሆን ኖሮ እኔም ብሆን ማንንም አልፈራም ነበር፡፡ ለምን ራሱ ዲያቢሎስም አይሆንም፡፡” ይሄኔ ዲያቢሎስ ከምድጃው ጀርባ አድፍጦ ይሰማው ነበርና ለራሱ እንዲህ ሲል ተናገረ፡፡ “አንተ እና እኔ እንግዲህ ይለይልናል፡፡ የተመኘኸውን መሬት ሁሉ እሰጥሃለሁ፡፡ ከዝያ የምትሆነውን አያለሁ፡፡” አንድ ምሽት የመሸበት ሲራራ ነጋዴ ፓሆም ቤት አረፈ፡፡ ለመንገደኛው ነጋዴ ሻይ ተፈልቶ እየጠጡ ሲጨዋወቱ፡፡ ሲራራ ነጋዴው ስለ አንድ ለም የሆነ ሸለቋማ አገር ይነግረው ጀመር፡፡ የዚያ ለም አገር ሰዎች ሰነፎች ከመሆናቸው የተነሳ ያንን እንደዳቦ የሚገመጥ መሬት ለማንም ሰው ከብላሽ በማይሻል መናኛ ዋጋ እንደሚሸጡ አጫወተው፡፡ ፓሆም ይህን ከሰማ በኋላ ሣይውል ሳያድር የቤቱን ነገር ለሚስቱ አደራ ሰጥቶ ከሚያምነው ወንድ አገልጋዩ ጋር ወደዚያ ሸለቆ ምድር ጉዞ ጀመረ፡፡ ለመንገድ ሲነሳ ለስጦታ ይሆን ዘንድ እንደ ሻሂ፣ ወይን ጠጅ፣ እና ሌላም ውድ ነገሮችን ይዞ ነበር፡፡ በዚያም አገር እንደደረሰ ስጦታውን ለተዋወቃቸው የለምለሙ ሸለቆ አገር ሰዎች ሁሉ እንደእጅ መንሻ እየሰጠ ስለመሬቱ ጉዳይ ይጠይቃቸው ነበር ፡፡ የአገሩ አውራ ሽማግሌ ለፓሆም እንዲህ አለው፡፡ “አንተ ለኛ ደግ ሰው በመሆንህ ያሻህን ያህል መሬት በአንድ ሺህ ሩብል ትገዛ ዘንድ ፈቅደንልሃል፡፡ ልብህ የፈቀደውን መሬት ያህል ዞረህ እንድትቸክልና እንድትመርጥ አንድ ሙሉ ቀን ሰጥተንሃል፡፡ ጠዋት ጀንበር ስትሰርቅ ጀምረህ ስትዞር ውለህ ጀምበር ስትጠልቅ የተነሳኸበት ቦታ ካልተመለስክ ግና መሬትህንም የከፈልከውንም አንድ ሺህ ሩብል ታጣለኸ፡፡ ነገር ግን ፀሃይ ከመጥለቋ በፊት ጉዞኸን ጨርሰህ ከጀመርክበት ቦታ የተመለስክ እንደሆን የደረስክበትና ችካልህን ያደረግክበት መሬት ሁሉ ያንተ ይሆናል፡፡” ፓሆም በሰማው ሃሣብ ፈነደቀ፡፡ ደስታውን መደበቅ ተሣነው ፡፡ ጨርሶ ሌሊቱን እንቅልፍ በአይኑ አልዞር አለ፡፡ አይኑን ሳይከድን በእጁ ስለሚያስገባው መሬት ሲቀይስና ሲቸክል ሌሊቱ ተገባደደ፡፡ ሊነጋጋ ሲል ፓሆምን እንቅልፍ ጣለው፡፡ ህልምም አየ፡፡ መሬት ላይ ወድቆ ከአንድ ሰው ጋር እየሳቀ ይመስለዋል፡፡ ታዲያ የሚስቀው ሰውዬ የቀዬው አለቃ ነበር፡፡ “ምንደነው የሚያስቅህ? “ ሲል ፓሆም ጠየቀ ፡፡ ይሄኔ የአገሬው አለቃ የመሰለው ሰውዬ ከሳምንታት በፊት ቤቱ ወደ አሳደረው ሲራራ ነጋዴ ተለወጠ፡፡ ቀጥሎ ከሲራራ ነጋዴው ወደ ሌላ ተለወጠ፡፡ ፓሆም የተለወጠው ሰው አልታይህ አለው፡፡ በምትኩ የሚስቅ ቀንድና ጭራ ያበቀለ ዲያብሎስ ሆነበት ፡፡ቀጥሎ መሬት ላይ የወደቀ ምስል ታየው ፡፡ እላዩ ላይ ምንም እራፊ ጨርቅ አልነበረም ፡፡ እግሩም ያለጫማ ነበር፡፡ ጠጋ ብሎ ሲመለከት የሞተው ሰው ለካ ራሱ ኖሯል፡፡ ይሄኔ ከህልሙ ብንን ብሎ ይነሳል፡፡ ጀንበር ገና መፈንጠቋ ነበር፡፡ ፓሆም መሬቱን መትሮ ለመቸከል ተቁነጠነጠ፡፡ የአገሬው አለቆች እጅ ሊነሱ ወደርሱ መጡ ፡፡ እናም የመነሻ ቦታው ላይ ምልክት አደረጉ፡፡ “እዚህ ነው መነሻ መደብህ ፀሃይ ከመጥለቋ በፊት ተመልሰህ መምጣት ከቻልክ ዞረህ ያካለልከው ሁሉ ያንተ ይዞታ ይሆናል፡፡” አሉት፡፡ ምልክት ካረጉበት መደብ ላይ 1ዐዐዐ ሩብሉን መደበ፡፡ እናም እየመተረ ችካልማድረጉን ወዲያው ጀመረ፡፡ ዙሪያ ገባውን የሚያየው ሁሉ የበለፀገ መሬት ነበር፡፡ ቀጠለ በየእርምጃው ምልክቱን እየተወ በተጓዘ ቁጥር ከአገሬው አለቆችና ከመነሻው ሥፍራ እየራቀ እየራቀ እነሱም ከአይን እይታ እየተሰወሩ ሄዱ፡፡ ጥቂት እረፍት አደረገና መልሶ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ቀጥ ብሎ ሳያወላውል በመሄድ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተጓዘ፡፡ ከዚያ ወደመነሻው የመልስ ጉዞውን ጀመረ፡፡ የተነሳበት ቦታ ላይ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ጨርሶ አይታዩትም፡፡ ፀሃይ ማዘቅዘቅ ጀምራለች፡፡ ወደመነሻው እየተመለሰ የቻለውን ያህል ተጉዞ በቂ መሬት እንዳገኘ ያስባል፡፡ እየተመለሰ ፀሃይ በፍጥነት በማዘቅዘቅ ላይ መሆኗን አስተዋለ፡፡ ከመነሻው በጣም ብዙ መራቁንም ተረዳ፡፡ እናም ፍጥነቱን ጨምሮ ገሠገሠ፡፡ “ፀሃይ ከመጥለቋ በፊት መድረሴን እንጃ፡፡ እንዲያ ከሆነ መሬቴንም አንድ ሺህ ሩብሌንም መቅለጤ ነው፡፡ “ እያለ ለራሱ አጉተመተመና ከእግሩ ነጠቅ ነጠቅ እያለ ግስጋሴውን አፋጠነ፡፡ የተሸከመውን ኮተት ሁሉ ወዲያ ወረወረ፣ ቀስበቀስም የለበሰውን ልብስ ሳይቀር አውልቆ ጣለ፡፡ ጫማውን ሳይቀር ከእግሩ አስወግዶ ባዶ እግሩን ሩጫውን ቀጠለ፡፡ ቀኑ እጅግ ሞቃት ነው ፡፡ አሁንም ግለቱ አልበረደም፡፡ ፓሆም ድካሙ ቢበረታም ሩጫውን አልገታም፡፡ “ወይኔ በጊዜው መድረሴን እንጃልኝ” ሲል ፓሆም አሰበ፡፡ ያለ የሌለ ሃይሉን አስተባብሮ በዚያ የሚቀቅል ሙቀት ሩጫውን አቀለጠው ፡፡ አሁን ሰዎች ሲጮኹና ሲያጨበጭቡለት ተሰማው፡፡ አንድ ሺህ ሩብሉን ያስቀመጠባት መደብ ሳትቀር ታየችው፡፡ አንዱ ሰውዬ ወደርሱ እያመለከተ ልክ በህልሙ እንዳየው አይነት በሳቅ ይንፈቀፈቃል፡፡ ልክ ገንዘቡን የመደበበት መደብ ላይ ዘፍ ሲል ፀሃይዋም አብራ ጠለቀች ፡፡ ሰዎቹ በጩኸትና በሙገሳ እያወኩ ባለበት እዚያው ቦታ ላይ ፓሆም ፍግም አለ፡፡ “ለራስህ የሚገባኸን ያህል መሬት በትክክል ለክተሃል፡፡ “አለ ዋናው ሰውዬ እናም ይኸን ብሎ ወደ ፓሆም ቀረበና እንዲነሳ ሊረዳው እጁን ዘረጋ፡፡ ፓሆም ግን አይንቀሳቀስም ነበር፡፡ የፓሆም ወንድ አገልጋይም እዚያው የወደቀበት መሬት ላይ መቃብር ቆፈረና ቀበረው፡፡ ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ የሚበቃ መሬት ነበር፡፡
test