የዶክተር ዝናሽ ስለሺ አጭር የሕይወት ታሪክ
Edited by : addiskignit@gmail.com -12/20/2022
ዶክተር ዝናሽ ከአባታቸው ከአቶ ስለሺ ደግፌና ከእናታቸው ከወይዘሮ ብርቱካን ደምሴ ሐምሌ 6 ቀን 1946 ዓ.ም በቀድሞ አጠራሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር በደብረዘይት ከተማ ነበር፡፡ ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ የነበሩት ዶክተር ዝናሽ አቅራቢያቸው ከሚገኘው ቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ከቆጠሩ በኋላ እስከ ሶስተኛ ክፍል ደግሞ በዚያው ደብረዘይት ልብነ ድንግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ፡፡ ከአራተኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተና እስኪፈተኑ ድረስ ደግሞ የአባታቸው እናት ወደ ሆኑት አያታቸው ወዳሉበት ይፋትና ጥሙጋ ሄደው ተምረዋል፡፡ የሚኒስትሪ ፈተናቸውን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቁ በኋላ በአካባቢው በቅርበ የሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ተመልሰው ወደ ደብረዘይት በመምጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአጥጋቢ ውጤት አጠናቅቀው በ1965 ዓ.ም አለማያ ግብርና ኮሌጅ ገብተው የእንሰሳት ሳይንስ መማር ጀመሩ፡፡ ዶክተር ዝናሽ የኮሌጅ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ በመሆኗ እና የሱማሌ ወራሪ ኃይል ጦርነት ስለከፈተ ከአለማያ ግብርና ኮሌጅ ወደ አዋሳ ግብርና ኮሌጅ ተዘዋውረው ለአንድ ዓመት ያህል እዚያው ተምረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ በነበሩበት ጊዜ የእድገት በህብረት ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ ወደ ወላይታ ሄደው ወገኖቻቸውን በትምህርትም ሆነ በልዩ ልዩ ማህበራዊ ተሳትፎ አገልግለዋል፡፡ በመጨረሻም በ1970 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመያዝ በቁ፡፡ ዶክተር ዝናሽ የግብርና ምርምር ስራቸውን የጀመሩት በ1971 ዓ.ም በቀድሞው የእርሻ መካነ ጥናት በአሁኑ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በእንሰሳት ምርምር መምሪያ በረዳት ተመራማሪነት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በሆለታ፣ በወረር፣ በባኮና በአዳሚቱሉ ይተገበር በነበረው የዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያ ክፍል ውስጥ የአራቱንም ማዕከላት መረጃ ወቅቱ በፈቀደው የመረጃ አያያዝ ስርዓት በማደራጀት፣ በመከታተልና ለማዕከላቱ ድጋፍ በመስጠት ለአገራዊ የዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ለአራት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ኢንስቲትዩቱ ባሳዩት ትጋትና ውጤት ስለተደሰተባቸው የተጨማሪ ትምህርት ዕድል ስለሰጣቸው ከዚያው በአለማያ ግብርና ኮሌጅ በ1977 ዓ.ም በእንሰሳት እርባታ ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በመያዝ በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል በእንሰሳት መኖና ስነ-ምግብ ዘርፍ በተመራማሪነትና ዘርፉን በመምራት አገልግለዋል፡፡ ዶክተር ዝናሽ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ውስጥ የነበራቸውን የሥራ አፈፃፀም እንዲሁም ለከፍተኛ ትምህርት ያላቸውን ፍላጎትና ተነሳሽነት በመገንዘብ ተቋሙ በሰጣቸው ከፍተኛ የትምህርት ዕድል በእንግሊዝ አገር በሬዲንግ ዩኒቨርስቲ በእንሰሳት ስነ-ምግብ ዘርፍ በ1987 ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት እንደተመለሱም ቀድሞ በነበሩበት ማዕከልና የሥራ ዘርፍ ተመድበው በከፍተኛ ተመራማሪነትና በአመራር ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን በአገልግሎት ዘመናቸው ከነበራቸው በርካታ አስተዋፅኦ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ለምርምር አቅም ግንባታ የሚውል ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀት ያበረከቱት አገራዊ አስተዋፅኦ Ø በሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል የእንሰሳት ስነ-ምግብ ቤተ ሙከራን በማደራጀትና በማዘመን Ø በሰው ኃይል ግንባታ በማደራጀት Ø ተስፋ ሰጪ የምርምር ውጤቶች በተጠቃሚዎች ሁኔታ እንዲገመገሙና ለተጠቃሚ እንዲደርሱ በማድረግ Ø በውጭ አገር የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ የምርምር ፕሮጀክት ዝግጅትና ትግበራ ላይ በመሳተፍ Ø የእንሰሳት ምርምር ዘርፍ ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል Ø በእንሰሳት ምርምር ዘርፍ ውስጥ ያሉ 10 ብሔራዊ የምርምር ፕሮግራሞችና በስራቸውም በርካታ የምርምር ፕሮጀክቶች በተለያዩ 40 የግብርና ምርምር ማዕከላት እንዲተገበሩ በማድረግ Ø በእንሰሳት ምርምር ዘርፍ በኢንስቲትዩቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ የምርምር ፕሮግራሞች የየራሳቸው ስትራቴጂክ እንዲኖራቸው የሚያስችል ሰነድ በማዘጋጀት ለ2020 የሚሊኒየም የልማት ግቦች መሳካት ከፍተኛ እገዛ በማድረግ Ø በእንሰሳት ዘርፍ የምርምርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትብብር እንዲጠናከር፤ የትምህርት ይዘቱም በአገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ እንዲያተኩር የሚያስችል የካሪኩለም ክለሳ በማድረግና የተማሪዎች የመመረቂያ ፕሮጀክቶችን በማማከር Ø በኢትዮጵያ የእንሰሳት እርባታ ባለሙያዎች ማህበርን በፕሬዘዳንትነት በመምራትና በሌሎች በርካታ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው የምርምር ስራዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ዶክተር ዝናሽ ሕይወታቸው በትምህርትና በስራ ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም፡፡ ከዚህ ይልቅ የሰው ልጆችን ሁሉ ሳያበላልጡ በማክበርና በመውደድ ጭምር የተጠመዱ ነበሩ፡፡ ከዶክተር ዝናሽ ጋር አብረው የመስራት አጋጣሚ የነበራቸውም ሆኑ የሚያውቋቸው ሁሉ የሚመሰክሩላቸው አንድ ባሕርይ ነበራቸው፡፡ እሱም ፍልቅልቁ ሳቃቸው ነበር፡፡ “ዝናሽን አይተሃል?” ተብሎ የሚጠየቅ ሰው መልሱ “አልሰማሁም” የሚል እንደነበር ይነገራል፡፡ ዝናሽ ካለች በአቅራቢያቸው ላለ ጭምር የሚተርፍ የፍስሐ ሳቅ ስለሚኖር! ነገሮችን አቅልለውና በፀጋ የመቀበል ከፍተኛ ችሎታ የነበራቸው ዶክተር ዝናሽ ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው የመመለስና ሁልጊዜም ቀና ልብና አስተሳሰብ ይዘው የኖሩ እንደነበሩ አብረዋቸው የኖሩ በአጠቃላይ በአንድ ድምፅ የሚመሰክሩላቸው ነበሩ፡፡ ስንደሌሎች አለቆች ትዕዛዝ ብቻ የሚያስተላልፉ ሳይሆኑ አብረው ሰርተው የሚያሰሩ ዘወትር ለአዲስ ነገር ዝግጁ የነበሩ መሆናቸውም ይነገራል፡፡ ከአዘነው ጋር የሚያዝኑት ከሚደሰተው ጋር የሚደሰቱት ዶክተር ዝናሽ አብረዋቸው ከሚሰሩ ጋር የቤተሰብ ያህል ቅርበት የነበራቸውና ለሌሎች ጉዳይ ትኩረት የሚሰጡና ፍቅርን በተግባር ያሳዩ ነበሩ፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆን አብረዋቸው ይሰሩ የነበሩ ሰው የተናገሩትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ “በአንድ ወቅት አንድ ዓለማቀፋዊ የማማከር ስራ ተወዳድራ አሸነፈችና ስራውን ጀመረችው፡፡ በኋላ ግን ወደ እኔ መጣችና ‹ይህንን ስራ አንተ ስራውና ገንዘቡን አግኝ፤ እኔ ያለኝ ይበቃኛል› አለችኝ፤ በጊዜው እኔ ቤት እየሰራሁ ስለነበር ‹ለቆርቆሮ መግዣ ይሆንሃል› ነበር ያለችኝ፡፡ ዝኒ እንዲህ ዓይነት ደግ ልብ የነበራት ናት፡፡” ነበር ያሉት፡፡ ዶክተር ዝናሽ ብዙ የሚባልላቸው ሚስት፣ እናት፣ እህት፣ ጓደኛ፣ የስራ ባልደረባ፣ ጎረቤት …ነበረች፡፡ ውድ ባለቤቷን ለመደገፍና ልጆቿንም በጥሩ ሁኔታ ለማሳደግ በመጣር መጽሐፍ ቅዱስ መልካም ሴት ብሎ የሚጠራት ሴት መሆኗን አስመስክራለች፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወቷም ጠንካራ እንደነበረች አብራቸው ያገለገሉ ሁሉ ይመሰክርሏታል፡፡
test