P 2 P ካናዳ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኂላ ለመጀመሪያ ጊዜ የራት ምሽቱን በታላቅ ድምቀት አካሄደ
Edited by : addiskignit@gmail.com -2/14/2023
ከ23 ዓመታት በፊት ለትውልድ አገራቸው ኢትዮጵያ ለመድረስ እና በኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ ተቋርጦ የቆየውን ዓመታዊውን የእራትና የገቢ ማሰባሰቢያ ምሽቱን በደማቅ ሁኔታ በዳንኤለ ስፔክትረም አዳራሽ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት አካሂዷል፡፡ ፒ2ፒ ካናዳ በኢትዮጵያ ላለፉት 23 ዓመታት ባደረገው ያልተቋረጠ ሰብአዊ ድጋፍና ርዳታ በርካታ ህፃናትን ወላጆቻቸውን ያጡ ታዳጊዎችን በማስተማር ለወግ ለማእረግ ያደረሰ ሲሆን አብዛኛውን ድጋፍ ለ17ዓመታት የሰጠው ህይወት የተቀናጀ የማኀበረሰብ ድጋፍ በተሰኘ አገር በቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አማካይነት ነበር፡፡ በሲስተር ጥበበ ማኮ መስራችነት የተቋቋመው ህይወት የተቀናጀ ድጋፍ ማዕከል ላለፉት 17 ዓመታት ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ከፒ2ፒ ጋር በመቀናጀት ሲያካሂድ ቆይቷል ፡፡ በዘንድሮው የእራት ምሽት ላይም ሲስተር ጥበበ ማኮ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ይኸንኑ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ ሲስተር ጥበበ የእለቱ ኪኖት ስፒከር የነበሩ ሲሆን ፒ 2 ፒ ባለፉት 17 ዓመታት ያካሄዳቸውን ዘርፈ ብዙ ድጋፎች በማድነቅ በካናዳ የሚገኙ የፒ 2 ፒ አጋሮች ስፓንሰሮችና ደጋፊዎች ወደፊትም ይኸን አጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ህፃናትና ሴቶች የተለያዩ ችግሮች ግንባር ቀደም ተጠቂም ስለሆኑ እንድረስላቸው ብለዋል፡፡ በእለቱ የቀድሞው የፒ2ፒ ኘሬዚዳንትና ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ ንጉሴ አዲሷን ኘሬዚዳንት ወ/ሮ ምስራቅ ልሣኑን በማስተዋወቅ ፒ 2 ፒ እንደተቂም በወጣቶችና በሴቶች የላቀ ተሣትፎና ችሎታ የሚተማመን በመሆኑ በርካታ ወጣቶችን በማሣተፍ የተለያዩ ሃላፊነቶችንና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን ሲያካሂድ መቆየቱን ጠቅሰው አሣቸው የሃላፊታቸውን ጊዜ ሲጨርሱ የተረከበቻቸው ምስራቅ ልሣኑ ፒ2ፒን በአመራር ብቃቷ ወደተሻለ ደረጃ እንደምታራምደው ያላቸውን እምነት ግልፀዋል፡፡ ወ/ሮ ምስራቅ ልሣኑ በበኩሏ ሃላፊነቷን ለመወጣትና በማኀበረሰበችን ችግሮች ላይ አተኩራ እንደምትሰራ ገልፃ ዘንድሮ በዚህ የራት ምሽት ላይ ታላቁን የኪነ-ጥበብ ባለሙያ አቤል ተስፋዬ ዘዊኬንድ ፒ2ፒን በመምረጥ የ5ዐ ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ይፋ አድርጋለች፡፡ በእለቱ አቶ ጊዮን ሸዋንግዛው የእጣ አወጣጥ ስነስርዓቱን ለተሣታፊዎች ይፋ ያደረጉ ሲሆን መድረኩን ደግሞ ወጣቷ ጋዜጠኛ ኤደን ደበበ አድምቃዋለች፡፡ በዳንኤል ባርነስ ኳርቴት ለስላሣ የጃዝ ሙዚቃ የታጀበው የዘንድሮ የፒ2ፒ የራት ምሽት በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ካናዳውያን የተሣተፉበት ነበር፡፡ ዝርዝሩን ከሰሞኑ በዩቲዩብ ቻናላችን ላይ ጠብቁን ፡፡
test