Views & Perspectives

ድርሳነ ሰማነህ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ የቀረበ የመጽሐፍ ዳሰሳ

Gezahegn Mekonnen Demissie·
Share
የአቶ ሰማነህ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ


የአቶ ሰማነህ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ተራ የግለሰብ ታሪክ አይደለም። የአንድ ሰው የሕይወት ጉዞ ሳይኾን የትውልድ ማስታወሻ ነው። የአገር መዝገብ ነው። ከገጠር የኢትዮጵያ ክፍሎች ተነስተው እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ የደረሱት የሚጋሩት ህያው የትውልድ ማስረጃ ነው።

 

መጽሐፉ አንድ ግለሰብ እንዴት በችግር ውስጥ ተፈትኖ እንደሚያድግ ያሳያል። ከወላጆቹ የተጀመረው ታሪክ፣ ወደ ልጅነት ተረኮች ያቀናል። የትምህርትና የተማሪ ቤት ትግል፣ የፖለቲካ ግፍ፣ የእስር ቤት ጥላ፣ የውጭ ሀገር ተሞክሮ፣ የዲፕሎማሲ ዓለም፣ የጦርነት ቀጠናዎች፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራ፣ የሃይማኖትና የማኅበረሰብ አገልግሎት እና መሰል ታሪኮችን በአንድ ሕይወት ውስጥ ያስቃኛል።

 

“ሕይወት ረጅም መንገድ ናት፤ ሰው ግን በሚያልፍባት መንገድ ይታወቃል” የሚባለውን አባባል በድርሳነ ሰማነህ መጽሐፍ ውስጥ ተመስክሯል። የመጽሐፉ ትልቁ ጥንካሬ የታሪኩ ስፋት ነው። ታሪኩ ከግለሰብ ሕይወት አልፎ የኢትዮጵያን የፖለቲካና የማኅበራዊ ለውጦች ይዳስሳል። የደርግ ዘመንን እስከነ-ቡጉሩ ተጽፏል። የአብዮት ዘመን ፍርሃትን በድርሳኑ ተከትቧል። የቻይናን የኮሚኒስት ሥርዓት ከውጪ ሳይኾን ከውስጥ ያሳያል። የአፍጋኒስታንን ጦርነት በተመድ ሠራተኛ ዓይን ይተርካል። ካናዳንም እንደ መጨረሻ የስደት ማረፊያ ብቻ ሳይሆን እንደ ዐዲስ የማንነት መስክ ያቀርባታል።

 

ይህ ታሪክ በአንድ ሰው ላይ ብቻ የቆመ አይደለም። የኢትዮጵያውያን የትውልድ ትርክት ነው። “ሰው ዘመኑን አይመርጥም፤ ዘመኑ ግን ሰውን ይፈትነዋል” የሚለውን ሐሳብ በግልጽ ያሳያል።

 

ከሥነ-ጽሑፋዊ አንጻር የመጽሐፉ አወቃቀር የሚስብ ነው። ክፍሎቹ በጊዜ ቅደም ተከተል ተደርድረዋል። ይህ አንባቢው የገጸ ባሕርዩን እድገት እንዲከታተል ያደርገዋል። ከ“ረዳት አልባው ወሊድ” እስከ “በካናዳ ፓርላማ” የሚደርሰው ጉዞ የማንነት ሽግግርን በጥልቅ ያሳያል። በመጀመሪያ የነበረው የገጠር ልጅ በመጨረሻ ዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚያነጋግር ሰው ይኾናል።

 

በዚህ ውስጥ የ“ሽግግር” ሐሳብ ትልቅ ቦታ አለው። ከገጠር ወደ ከተማ። ከኢትዮጵያ ወደ ዴንማርክ። ከዴንማርክ ወደ ቻይና። ከቻይና ወደ አፍጋኒስታን። ከጦርነት ወደ ሰላም። ከፍርሃት ወደ ተስፋ። ይህ ሁሉ ታሪኩን የከፍታና የዝቅታ፣ እንዲሁም የእውቀት ጉዞ ያሳያል።

 

በተለይ የቻይና ምዕራፎች በጣም አስደሳች ናቸው። ኢትዮጵያዊ ተማሪ በማዖ ዘመን ቻይና ያየውን ሲተርክ አጃኢብ ያሰኛል። ይህ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በሩቅ ምሥራቅ የነበራቸው የተማሪ ቤት ሕይወትን በጉልህ የሚያሳይ ታሪካዊ ሰነድ ነው። በተለይ “ከቻይና እና ማዖ ሴቱንግ ጋር ትውውቅ” እና “የቻይናን ታላቅነት የመረዳት ጅማሮ” የሚሉት ምዕራፎች የፖለቲካ እውቀትን ከግል ተሞክሮ ጋር ያጣመሩ ናቸው። የቻይና ክፍሎች ታሪካዊ ክብደት አላቸው። አንድ ኢትዮጵያዊ ተማሪ በማዖ ዘመን ቻይናን ከውስጥ ሲመለከት የሚያቀርበው ዕይታ በዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ብርቅ ነው። በተለይ “የቻይናን ታላቅነት የመረዳት ጅማሮ” የሚለው ርዕስ፣ የባለታሪኩን የዓለም ዕይታን የመዘገብ አቅም እንድናደንቅ ይጋብዛል።

 

አቶ ሰማነህ የተመድ ሠራተኛ ኾኖ በአፍጋኒስታን የነበረው ቆይታ በመጽሐፉ ውስጥ በስፋት ተካቷል። እነዚህ የአፍጋኒስታን ክፍሎች እጅግ ልብ አንጠልጣይ ናቸው። ከታሊባን ጋር በነበራቸው አንዳንድ ስብሰባዎች መካከል የሚከሰቱ ነገሮች ልብን ሰቅዘውና ቆንጥጠው የመያዝ አቅም አላቸው። የአፍጋኒስታን ምዕራፎች መጽሐፉን ከተራ የስኬት ታሪክ ያሻግሩታል። በታሊባን መካከል መኖር፣ ሞትን በቅርብ ማየት፣ በእምነት ላይ ፈተና መጋፈጥን ምን እንደሚመስል በሚገባ ያንጸባርቃል። እነዚህ ሁሉ የሰው ልጅ ውስጣዊ ጥንካሬን ይፈትናሉ። በዚህ ቦታ መጽሐፉ ጀግንነትን በተመለከተ ዐዲስ አተያይ ይሰጠናል። ባለታሪኩ ጀግና ነው፤ ግን ከፍርሃት ነጻ አይደለም። የሚገርመው ይህ ነው። ጀግንነቱ በፍርሃቱ ውስጥ ነው።

አቶ ሰማነህ በሙጅሃዲን የታገተበት ክፍልም አስደንጋጭና ልብ የሚያንጠለጥል ክፍል ነው። እንደ በሰርግ ላይ ጫማ መሰወር የሚመስሉ ትንንሽ ትዕይንቶች እንኳን ታሪኩን ሕያው ያደርጉታል። ታሪኩ በዓለም ፖለቲካ መካከል የቆመ ሰው ውስጣዊ ስሜትን ያሳያል።

 

መጽሐፉን በክፍል በክፍል ማየት ለሚፈልግ እጅግ ብዙ ነገሮችን ማለት ይችላል። ለዚህ ጽሑፍ እንዲኾን ግን መጽሐፉን በሦስት ዋና ዋና መስመሮች እንመልከተው።

 

አንደኛ

የእድገት ታሪክን በሚገባ ቀርቧል። አንድ ልጅ በልምድ እየተፈተነ ወደ ሙሉ ማንነት የሚያድግበትን ጉዞ መጽሐፉ በሚገባ ያሳያል።

 

ሁለተኛ

እንደ ድኅረ-ቅኝ ግዛታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥራ መነበብ ይችላል። የዴንማርክ ተረክ - የምዕራቡን፣ የቻይና እና የአፍጋኒስታን ቆይታው - ምሥራቅን፣ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ - አፍሪካን እንዲሁም የአሜሪካ እና የካናዳ ታሪኮችን በአንድ ሕይወት ውስጥ ያገናኛል። የባሕል ግጭትን፣ የማንነት ጥያቄን፣ የስደት ሥነ-ልቦናን ያቀርባል። መጽሐፉ ድኅረ-ቅኝ ግዛታዊ የሥነ ጽሑፍ አተያይ ለመተንተን ሰፊ እድል ይሰጣል። ባለታሪኩበምዕራብና በምሥራቅ መካከል ይጓዛል። ከ“ነጮች” ጋር ያለው ግንኙነት፣ በቻይና ያገኘው ዐዲስ የዓለም ዕይታ፣ በተመድ ያለው ዓለም አቀፍ ልምድ ... እነዚህ ሁሉ አንድ አፍሪካዊ ራሱን በዓለም እንዴት እንደሚያይና እንደሚያሳይ ምሳሌ የሚኾን መጽሐፍ ነው።

 

ሦስተኛ

እንደ እማኝያዊ ሥነ ጽሑፍ ይህን መጽሐፍ መመልከት ይቻላል። የግፍ ዘመንን በሕይወት ያለፈ ሰው የሚያቀርበው የምስክርነት መጽሐፍ ነው። የእስር ቤት ልምዶች፣ የፖለቲካ ጭቆና፣ የጦርነት ጥላዎች … ሁሉም የታሪክ ማስረጃ ይኾናሉ።

 

የመጽሐፉ ትልቁ ጥንካሬ ውስብስብ ጉዳዮችን ለሁሉም ሰው እንዲኾን ተደርጎ መቅረቡ ነው። ምዕራፎቹ ከባድ የአካዳሚ ቃላትን ሳይጠቀሙ ጥልቅ የኾኑ ሐሳቦችን ግን ያቀርባሉ። ይህ መጽሐፉን ለምሁርም ለተራ አንባቢም ተደራሽ ያደርገዋል። “ጥልቅ ውኃ ጸጥ ይላል” እንዲሉ፣ ትልቅ ልምድ በተረጋጋ አነጋገር በዚህ መጽሐፍ ላይ ይስተዋላል።

 

ይህ የአቶ ድርሳነ ሰማነህ መጽሐፉ የተስፋ መጽሐፍ ነው። በችግር ውስጥ ያለች መውጫ ቀዳዳን ብዙ ቦታ እናገኛለን። ለአንባቢውም ተስፋን ይሰጣል። በገጠር ተወልዶ ዓለም መድረክ መድረስ እንደሚቻል ያሳያል። ትምህርት የሕይወት መለወጫ መኾኑን በገደምዳሜው ያስረዳል።

 

ይህ መጽሐፍ “ታሪክ ለማስታወስ” ብቻ የተጻፈ አይደለም። “ትውልድ እንዲማር” የተጻፈ ነው። የአቶ ሰማነህ ሕይወት ከግል ስኬት በላይ የጽናት ምሳሌ ነው። ከአንዲት የኢትዮጵያ ክፍል ተነስቶ ዓለምን የዞረ ሰው ታሪክ ነው። “ሰው ሲሞት ታሪኩ ካልተጻፈ ሁለት ጊዜ ይሞታል” ይባላል። ይህ መጽሐፍ ግን አንድ ሕይወትን በቃል ያባዛል። እንኳን ተጻፈ ያሰኛል።

 

መጽሐፉ የሚያነሳቸው ርዕሶች ጥልቅ የኾነ ሥነ-ጽሑፋዊ እና ታሪካዊ ክብደት አላቸው። ይህ መጽሐፍ “እኔ ማን ነኝ?” የሚለውን ጥያቄ ብቻ አይጠይቅም፤ “አገር ሰውን እንዴት ትሠራለች?” የሚለውንም ይጠይቃል እንጂ።

 

በሥነ-ጽሑፋዊ አተያይ፣ መጽሐፉ ግለ-ሕይወት ታሪካዊ ዘውግ ቢኾንም አቀራረቡ በደንብ ሲጤን የጉዞ ትርክት ባሕርይንም አዝሏል። ባለታሪኩ ከኢትዮጵያ ገጠር ይነሳል። ከዚያ ወደ ዓለም ይጓዛል። ዴንማርክ ይሄዳል። ቻይናን ከእግር እስከራሷ ያያል። ይኖራል። አፍጋኒስታንን እስከ ክንብንቧ ያስቃኘናል። ካናዳ ያርፋል። ይህ ጉዞ የቦታ ጉዞ ብቻ አይደለም። የአስተሳሰብ ጉዞ ነው። የማንነት ጉዞ ነው። የፖለቲካ ንቃተ ሕሊና ጉዞ ነው። “ሰው ካልሄደ አያውቅም” እንዲሉ፣ ባለታሪኩ ዓለምን እያየ ራሱን ይረዳል።

 

የመጽሐፉ ትልቁ ጥንካሬ የታሪክና የግል ሕይወት መጣመሩ ነው። ድርሳነ ሰማነህ ላይ ባለታሪኩ በታሪክ መካከል ቆሞ እናየዋለን። የደርግ ዘመን፣ የአብዮት ሽብር፣ የማዖ ቻይና፣ የአፍጋኒስታን ጦርነት፣ የ9/11 ክስተት … እነዚህ ሁሉ ከባለታሪኩ የግል ትዝታ ጋር ተጣምረዋል። ይህም፣ መጽሐፉን የግል ትዝታ ብቻ ሳይሆን የታሪክ ሰነድ ያደርገዋል።

 

“እፉኝቱ አብዮት እና እኔ” በሚለው ክፍል ላይ የሥነ-ልቦናዊ አተያዮችን እንድንመለከት ምቹ አጋጣሚ እናገኛለን። እስር፣ ፍርሃት፣ ጥርጣሬ፣ የሞት ጥላ፣ የአባት ሞትና ጸጸት … እነዚህ ሁሉ የባለታሪኩን ውስጣዊ ስብራት ያሳያሉ። አንድ ሰው በፖለቲካ ማዕበል ውስጥ እንዴት እንደሚፈተንም ኹነኛ አስረጅ የኾነ ክፍል ኾኖ እናገኘዋለን።

 

መጽሐፉ የህላዌነት ጉዳይንም ያነሳሳል። የህልውና ጭንቀትን ይጠቁማል። “ለምን እኖራለሁ?” “ለምን ተረፍሁ?” የሚለውን ጥያቄ ውስጡ ይሸከማል። “ከሞት ወደ መሰንበት” የሚለው ርዕስ ብቻ እንኳን ይህን ያሳያል።

 

መጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው ንዑስ ርዕሶቹ ከውበታቸው በተጨማሪ በራሳቸው ታሪኩን ይናገራሉ። “ባቡርና አውሮፕላን ቆሞ አይጠብቅም”፣ “በሰርግ ላይ የተሰወረው ጫማዬ”፣ “እሥረኛው እሥረኛ ሲጠይቅ” የሚሉት ርዕሶች አንባቢን የሚስቡ ናቸው። የንዑስ ርዕስ አወጣጡ ከቃላዊ ትርክት ጋር ይመሳሰላሉ። ልክ እንደ ፈሊጥ፣ ልክ እንደተረትና ምሳሌ ልክክና ስክክ ያሉ ናቸው።

 

በአጠቃላይ፣ ይህ መጽሐፍ የአንድ ሰው ሕይወት ብቻ ሳይሆን የአንድ ትውልድ ታሪክ ነው። ከገጠር ወደ ዓለም የወጣ ኢትዮጵያዊ የማንነት ጉዞ ነው። የትምህርት ኃይልን፣ የጽናት ዋጋን፣ የታሪክ ግፍን፣ የሰው ልጅ የመቋቋም አቅምን ያሳየ መጽሐፍ ነው። “እሳት ያላየ ወርቅ አይጠራም” እንዲሉ፣ የአቶ ሰማነህ ሕይወት በፈተና ውስጥ የተቀረጸ ነው።