አምስት አመታት ለቅፅበት ለመተያየት!! -ሶስና አሸናፊ
Edited by : addiskignit@gmail.com -8/12/2023
የናፍቆት ቀናቶች ይበርዳሉ። በመኖርና ባለመኖር መካከል ይጥላሉ። አንዴ ደስታ አንዴ ሀዘን አንዴ ሳቅ አንዴ ስጋት እየተፈራረቁ ውስጥን በጭንቀት ይነድላሉ። በተለይ የምትሳሱለት ከሆነ፤ እረጅም እድሜ እንዲኖር፣ እጁን ቁርጥማት እንዳይነካው በእድሜው ሙሉ ጤናና ደስታ እንዲያገኝ ከተመኛችሁ? እሱ ደግሞ ተራውን ጅንን ፣ኮስተር ካለ እንደኔ ከሱ ፊት ለፊት በኩራት ለመቆም ትመኛላችሁ። እኔማ አይኑን በአይኔ ለማየት እጁን በእጄ ለመዳሠሥ አምስት አመት ጠብቄያለሁ። ስራዎቹ ውስጥ አግኝቼዋለሁ። ጠይቄዋለሁ፣ ሞግቼዋለሁ። ግን የምንኖርበት ሀገር ወዲህና ወዲያ በመሆኑ የቅርብ እሩቅ እንደሚሉት መገናኘታችን ራቀ። አቤት የቀኑ ርዝማኔ ቶሎ አይመሽ ቶሎ አይነጋ ። ስንገናኝ እጅለእጅ ተያይዘን በጎዳናዎቹ ላይ የሚጣፍጥ ጨዋታውንና የእውነት ሳቁን አብሮ ለመሳቅ ፣ ስሩ ገብቼ የሚናፈቀውን ወጉን ለመኮምኮም። በሱ ልጅነት ውስጥ ልጅነቴን፣ ለማስታወስ ፣በሱ የፍቅር ወግ ውስጥ ደግሞ ፍቅሬን ለማስታመም ጊዜውን በቻልኩት መጠን በመንሰፍሰፍና ስንገናኝ እንዴት ሰላም እንደምንባባል በማሰብ ገፍቼ የቀጠሯችን ቀን አደረስኩት። ድምፁ የበለጠ ናፈቀኝ። ፊቱ መቆም አጓጓኝ።የሀገሩን እርቀት የአኗኗር ዘይቤውን በመርሳት ታቁታላችሁ? ብዬ መጠየቅ ጀመርኩ። "እሱ ማነው ?" አሉኝ "እሱማ . . እያልኩ ስለሡ ነገርኳቸው። ረጅም ነው። ቆንጆ፣ሳቂታ፣ጨዋታ አዋቂ፣ የፍቅር ሰው ደግሞም የሀገር ሀብት። ደግሞም ታዋቂና ተወዳጅ" "እሱ?" "አዎን ቤቱ ከዚህ ይርቃል?" ተንሰፈሰፍኩ "ላይርቅ ይችላል። አድራሻውን ይዘሻል?" "አድራሻው?" ስልኬን ብድግ መልሼ ቁጭ ።እንደገና ብድግ መልሼ ቁጭ ከዚያ " የስራ ቦታውስ?" "አድራሻ. . አድራሻውን ንገሪና" አድራሻ አድራሻው አንዱን ትቼ ሌላውን እጠይቃለሁ። በኦታዋ ቆይታዬ ላገኘሁት ሁሉ የማቀርበው ጥያቄ ሆነ። ቤቱ የት ነው ? ቅርብ ነው ሩቅ? ትእግስት በማጣቴ እራሴን ታዘብኩት። ካለሁበት ሀገር አምስ መቶ ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዤ እሱን ለማየት መምጣቴን ሳስበው ኩራት ተሠማኝ ። የሚወዱትን ለማግኘት መጓጓት እንዴት ደስ ይላል።ብዬ ራሴን አፅናናሁት። እሱ የሚወደውን ሻሽ ሸብ አድርጌ ካለሁበት ወጣሁ። ከመጣበት አቅጣጫ ለመያዝ አራት መንታው ላይ ቆምኩ። ሳየው ልቤ ፈሰሰ. . ዓይኖቹ ብር ብለዋል። እቅፍ አረገኝ፣ እቅፍ አደረጉት። የፀጉሩን መሸበት ሳይ ሳሳሁለት። እጆቹን ደጋግሜ አየኋቸው። ዳበስኳቸው። ፊቱ ድካም አርግዟል። አለባበሱ እንደነገሩ ሆኖ ያሳብቃል። መልሼ አቀፍኩት። "እንኳን አገኘሁሽ?" ". ደህና ነህ? የማንገናኝ መሥሎኝ አዝኜ ነበር" አልኩት "እኔም እስካይሽ ቸኩዬ ነበር" "እኔ እምልህ?" "አንቺ የምትይኝ" ቀልዱን ጀመረ ሲጣፍጥ። "ባንገናኝስ?" "እሱን ነበር ሳስብ የነበረው" "በሀዘን የምሞት ይመሥለኛል" አልኩት። ከደጃፉ ደርሼ ሳላገኘው ብመለስ። መከፋቴ አይኔ ላይ ተንጠለጠለ። ኮስታራነቱ ጥሎት ጠፍቷል።አስፈሪው ግርማ ሞገሱ የለም። ስስ ሆነብኝ አሳቢና ተጨናቂ። ሙሉ ሳቅ ፣ሙሉ ጨዋታ። አልዘለቀም ድንገት ከመቀመጫው ብድግ ብሎ አቀፈኝ አቀፍኩት። "በቃ ልትሄድ ነው?" ልቤ ተከፈለ። "መቆየት አልቻልኩም" በአይኔ ተከተልኩት። የአምስቱ አመት ጥበቃ አይንን ከፍቶ በመክደን መሀል ቆይታችን ተጠናቀቀ። ልቤ ተገምሶ የወደቀ መሠለኝ። ቀልቤም አካሌም ከሱ ጋር ነጎደ። ለምን አልሸኘሁትም? ውስጤን ጠዘጠዘኝ። ጥያቄዬን ሳልጨርስ እግሬ መራመድ ጀምሯል። ደግሜ እንዳቅፈው፣ እንድስመው ፣ እንዳወራው ግን አልደረስኩበትም መኪናውን አስነስቶ ወደቀኝ ታጠፈ። ሀዘን ፀጉሬን እየሠነጠቀ በአናቴ ሲገባ ፤ ሰውነቴ እንደደረቀ መሬት ተሠነጣጠቀ። ልቤ ከሱ ጋር እግሬ ከመሬቱ ጋር ተጣብቆ ቀረ። Aug 3/2023 ከኦታዋ ወደ ቶሮንቶ ባቡር ውስጥ
test