News

የአዲስ ቅኝት ቲቪ አንደኛ ዓመት የመጨረሻው ዙር የሥነ ጽሑፍ ተወዳዳሪዎች ተለዩ

Gezahegn Mekonnen Demissie·
Share
የአዲስ ቅኝት ቲቪ የመጨረሻው ዙር የሥነ ጽሑፍ ተወዳዳሪዎች ተለዩ

የአዲስቅኝት ቴሌቪዥንን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተክለሚካኤል አበበ ህግ ቢሮ ሸላሚነት የሚካሄደው የሥነ ጽሑፍ ውድድር የመጨረሻ ተወዳዳሪዎችን ለይቷል ።

የመወዳደሪያ ሥራቸውን ካቀረቡ ተወዳዳሪዎች መካከል ስምንት ድርሰቶችም ለመጨረሻ ዙር ማለፋቸውን የሥነ ጽሑፍ ውድድሩ ዳኞች ለአዲስ ቅኝት ገልፀዋል።

የሥነጽሑፍ ሣሎን መሥራቾች ከተክለሚካኤል አበበ TAS LAW ተቋም ጋር በመተባበር ለአዲስ ቅኝት ቲቪ አንደኛ አመት ባዘጋጀው በዚሁ ውድድር 35 ተወዳዳሪያን በተገደበው ጊዜ ሥራቸውን ያቀረቡ ሲሆን መሥፈርቱን ያሟሉት ውድድር ውስጥ ተካትተዋል።

 አጭርና የአጭር አጭር ልብወለድ የአጻጻፍ ሕግና ደንብ ተከትለው እንዲጽፉ በሚጠይቀው በዚህ ውድድር ግጥሞችና ወግ የጻፉ ተወዳዳሪዎች የውድድሩን ሕግ ባለማሟላታቸው ከውድድር የወጡ ሲሆን ቀሪዎቹ ለውድድር ተለይተዋል።

 በሦስት ዳኞች ሲገመገም የነበረው የሥነጽሑፍ ውድድር ስምንት ተወዳዳሪዎችን በመለየት ለመጨረሻ ዙር ያበቃ ሲሆን ከስምንቱ ሦስቱ ለደረጃ የሚቀርቡ ይሆናል።ይህም የአዲስ ቅኝት ቴሌቪዥን አንደኛ ዓመት በሚከበርበት ዕለት ማለትም ኦገስት 29 ቀን 2026 በ515 ብሮድቪው አቬኑ ቶሮንቶ ውስጥ ይፋ ይሆናል ተብሏል።

አንደኛ ለሚወጣ ተወዳዳሪ የ50 ሺህ ብር ሽልማት በሚያጎናጽፈው በዚህ ውድድር ከፍተኛ ፉክክር የታየ ሲሆን ተወዳዳሪያን ለሰጡት ፈጣን ምላሽ የአዲስ ቅኝት ቲቪ እና የሥነ ጽሑፍ ሳሎን መሥራቾች ምሥጋና አቅርበዋል።

 ኦገስት 29 ቀን 2026 ለሚከበረው የአዲስ ቅኝት ቴሌቪዥን አንደኛ ዓመት ልዩ ዝግጅት ከ1-3 የወጡ ተወዳዳሪዎች ደረጃቸውና ያሟሉት መሥፈርት ተገልጾ ሽልማታቸውን የሚወስዱ ይሆናል።