
ቶሮንቶ -ዲሴምበር 9፣ 2025 — በታላቁ የቶሮንቶ እና አካባቢው የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ማህበር በጃንዋሪ 25 ቀን 2026 በጉጉት የሚጠበቀውን ምርጫ ለማካሄድ ቁልፍ የአመራር ለውጦችን እና የመልካም አስተዳደር ለውጦችን ማካሄዱን አስታውቋል።
የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ባወጣው መግለጫ ባለፉት ሶስት አመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጎልበት ባለፈው ኖቬምበር 30 ቀን 2025 ያካሄደውን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ተከትሎ የውስጥ አስተዳደርን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ቦርዱ በጉባኤው በተነሱ የህግ ትርጉም ጉዳዮች ላይ የህግ ባለሙያዎችን እያማከረ መሆኑን ገልጿል። የተነሱትን ስጋቶች ለመፍታት እና ከምርጫው በፊት መስተካከል ያለባቸውን
ችግሮች በማረም የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ በጃንዋሪ 25 ቀን 2026 እንደሚጠራና ምርጫውን ህጉ በሚለው መሰረት ለማካሄድ ወስኗል።
የአመራር ሽግግሩ አንዱ አካል የሆነውና ቦርዱን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ዳዊት በየነን መልቀቂያ በይፋ ተቀብሏል። አቶ ደምሰው ተፈሪ በምትኩ የምክትል ፕሬዝዳንትነት ሃላፊነትን ተረክበው እንዲሰሩ ተሹመዋል። የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በተጨማሪም አቶ ፈንታው አባተን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሆነው እንዲያገለግሉ ሾሟል።
ቦርዱ ለአቶ ዳዊት በየነ ለድርጅቱ ላበረከቱት አስተዋጾ የላቀ ምስጋናውን ገልጿል።
ግልጽነትን ለማጎልበት እና ከማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ጋር ለማጣጣም በርካታ የአሰራር ማሻሻያዎችም እንደሚካሄዱም አስታውቋል ከእነዚህም መካከል
የሚከተሉት ተካተዋል:-
በስልክ፣ በኢሜል እና በማህበሩ ድህረ ገጽ የአባላትን ተደራሽነት በማስፋት ጥሪ ማድረግ
በህጋዊ መስፈርቶች መሰረት የአስመራጭ ኮሚቴውን በአምስት አባላት መገደብ።
እነዚህ ለውጦች መሰረት በማድረግ ቦርዱ ጃንዋሪ 25 ቀን 2026 ሊደረግ ለታቀደው ምርጫ የሚካሄድበትን ትክክለኛ ጊዜና ቦታ በቅርቡ እንደሚገለጽ አሳውቋል።