ጊዜ-ሶሶና አአሸናፊ
Edited by : addiskignit@gmail.com -3/18/2023
ሰፊው ሣሎን ውስጥ የተሰቀለው የግድግዳ ሰዓት ፍጥነት ጨምሮ አቶ አስናቀ ጆሮ ላይ ያስተጋባል፡፡ “አርፈው አይተኙም? እሱ እንደሆን መምጣቱ አይቀር፡፡ እርሶስ የት ይሄዳሉ? ምን ያጣድፋል?” አለቻቸው፤ ሠራተኛቸውም የልጃቸውም እናት የሆነችው አሰለፈች ወፍራም ቂጧን እያንደባለለች፡፡ “እንዴት?” በደከመ ድምጽ ጠየቋት፡፡ “እንደው ከወትሮው ለየት ብለው ተጣደፉ ብዬ ነዋ!” “እኔስ ቀጠሮ እንዳለኝ ማን ያውቃል?” “ቢሆንም . . ቢሆንም በዛ፡፡ እሱ እንደሁ ጓደኞቼ እንዳያመልጡኝ ልድረስባቸው ብሎ ነበር ሲከንፍ የሄደው” አለች፤ በመጨነቅ ሁለት እጅዋን እንደ ልጅነቷ እያፋተገች፡፡ “የሞት ቀጠሮ ነው?” አሉ፤ በምግብ የበለዘ ጥርሳቸውን ገልጠው ፊት ለፊት ከተሰቀለው ጎረምሣ ልጃቸው ፎቶ ላይ እያፈጠጡ፡፡ “ካልሆነ እኔው ልሞክርልዎት ምን ፈልገው ነበር?” አለች ንቅሣት ያስረዘመው አንገቷን አስግጋ “አንቺ በሱ ስም ስንቱን ትሞክሪያለሽ አሁንማ ቤቱን ሞላው እኔ ነኝ አዛዥ የቤቱ ባለቤት ሊል ምንም አልቀረው” አሉና ቀሪውን ለራሣቸው አጉረመረሙት አቶ አስናቀ ሰማንያ ዓመት ሆኗቸው አልጋ ሣይዙ “ሚስት ማግባት ጉልበት መጨረስ ነው” እያሉ በሠራተኛ የኖሩ ሰው ናቸው፡፡ አሁን እንኳን እርጅና ከሕመም ጋር ተጨምሮ ጉብዝናቸውንና አቅማቸውን ሰልቦ አልጋ ላይ ቢያውላቸውም እጅ ላለመስጠት እየታገሉ ነው፡፡ አግራቸው መቆም አቅቶት |ሲጥመለመል. . “አይዞህ በርታ” ይላሉ ለራሳቸው፡፡ “የሚቀመስ ላምጣ? ምነው ዛሬስ አልህ ተጋብተዋል፡፡ ይኸው የረባ ምግብ ሣይበሉ ሶስት ቀኖት ” አለች ፀባያቸውን ማስታመም የሰለቻት ሠራተኛ፡፡ “አንቺን ልጠይቅሽ እንጂ! ምነው ከኔ ጋር ሮጥሽ?” አሉና ግድግዳው ላይ ከረባትና ኮት አድርጎ የተነሣው ልጅ ፎቶ ላይ አፈጠጡ፡፡ የልጃቸውን ደረስኩ ደረስኩ ማለት መቀበል አቅቷቸዋል፡፡ ቁጭት አይሉት ንዴት ባዩት ቁጥር ያንገበግባቸዋል፡፡ እንደውም “ ስማ እኔ እንዳንተ ደልቶኝ አልኖርኩም ማጅራቴን እያሣበጥኩ አልንገላወድም አምስት መርፌ አምስት ሣንቲም እያልኩ ነው ያደኩት እኔን ካላገለገልከኝ ምን ትሰራልኛለህ ደግሞስ ቤቴንና ገንዘቤን ለመውረስ ያምርሃል ዋ! ዋ!” “አባባ ምን እያልክ ነው አልገባኝም፡፡ የኔን ጓደኞች አላየሃቸውም ስንትና ስንት ነገር እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል፡፡ እኔ ምን ተደረገልኝ እስኪ ንገረኝ” ቢጎሻምቱትም ከመጠየቅ አይቦዝንም፡፡ “ከኔ መወለድህ ብቻ ይበቃሃል ፡፡ ከፈለኩኝ ልጅነትህን እክዳለሁ፡፡ ማን ይጠይቀኛል ፡፡ ወለድኩ ብል አልወለድኩ ብል መብቱ የኔ ሰማህ ? “ ጠረጴዛውን በቡጢ መትተው ንግግሩን ሣያስጨርሱት ይወጣሉ፡፡ “እማዬ አባባ ለምን እንደልጁ አያየኝም ሁል ጊዜ ጥጋበኛ እንደሆንኩ ነው የሚሠማው” እያለ እሱም በተራው እናቱ ላይ ይጮኻል፡፡ “ነገሩ ወዲህ ነው ልጄ ትለዋለች በደፈናው ለሱ የማይነገሩትን የአባቱን ፀባይ እያሽሞነሞነች፡፡ “አንቺና እሱ እንዴት ተገናኛችሁ እስኪ ንገሪኝ ማወቅ እፈልጋለሁ ወይ ላንቺ ወይ ለኔ ክብር የለው፡፡ የሁል ጊዜ ጥያቄው እና ጉርምርምታው ነው፡፡ “ክብር” አለች ድምጿን ቀንሳ፡፡ ከዚህ ሌላ አትናገርም፡፡ ግን ታስበዋለች፤ እሱን ወልዳ ማዕድ ቤት ተኝታ የአራስ ጊዜዋን እንዴት እንዳሳለፈች፡፡ ደግሞ ይጠይቃታል “ከየት መጣሽ?” “ነገሩ እንዲህ ነው እናቴ ስትሞት አባቴ በአደራ ሠጧቸው አስተምራለሁ አሣድጋታለሁ ብለው ወሰዱኝ፡፡ አባቴ ሲሞቱ ነገሩ ሌላ ሆነ ሠራተኛም የአንተም እናት ሆንኩኝ፡፡” ትለዋለች ፊቷ እየተለዋወጠ፡፡ የሰማውን ሰምቶ ጮሆ መልስ ሲያጣ አንገቱን እንዳቀረቀረ ግራ በተጋባ ሁኔታ ቤቱን ጥሎ ይወጣል፡፡ “ምነው ሐሣብ ገባሽ? “ አሉ አቶ አስናቀ የሰራተኛቸውን መፍዘዝ በደንገዝጋዛው እያዩ “እንደው የርሶ ነገር ነዋ፤ አህልም የማያስቀምስ ምን ነገር ገጠምዎት ብዬ ነዋ ይህን ሣምንት ተይዘዋል ምን አለ ከሀኪም ዘንድ ብንሄድ ወይ የንሰሀ አባቶን ልጥራ አፎት ይደርቃል ፣ ያተኩሶታል፣ ምግብ እቢ አሉ ተይዘዋል ጨነቀኝ እኮ አንቱ!”አለች አንገቷን ከግራ ወደቀኝ እየመለሰች “አቤት ለኔ አስበሽ ሞተሻል! ደግሞስ እህል ስንት ዓመት ሊያኖረኝ?” “ወይ እርስዎ የዛሬውስ ብስዋል አይኖት እኮ ግሽርጥ መስሏል፡፡ ” “ፀጉሬን ጥፍሬን ጢሜን እንዲቆርጥልኝ እፈልጋለሁ እሱ ግን ማን አለበት እሱን ያሣደኩበትን አንድ ወጠምሻ ብቀጥር ቀጥ ለጥ ብሎ ያኖረኝ ነበር ፡፡ ምን ዋጋ አለው ውሻ ከሄደ ጅብ ጮኸ ነው፡፡” አሉና ልጃቸውን ማሠብ ጀመሩ፡፡ እያናገሩት ትቷቸው መውጣቱን በአእምሮአቸው አመላለሱት፡፡ ሲበላ ሲለብስ መንቀዥቀዥን አዩት “ቀልበቢስ” ለራሣቸው ነገሩት፡፡ እንደገና አሰቡት በሁለት ጉንጩ ወጥሮ ሲያላምጥ ወዲያው ፀጉሩን ሲደባብስ ሱሪውን ከፍ እያደረገ ሲንጎራደድ አይውጡት አይተፉት ነገር ጉሮሮአቸው ላይ ተሰነቀረ፡፡ “አባባ ያልከኝን ነገር አደርጋለሁ፡፡ ጓደኞቼ እንዳያመልጡኝ ልሂድ፡፡ ቀጠሮ አለኝ ነገ ቀኑን ሙሉ ከአንተ ጋር ነኝ፡፡” ቀይ ፊቱ ደም እስኪመስል ፊቱን እያሸ በቀኝ ትከሻው ላይ ጃኬቱን አስቀምጦ ስልኩን አንጠልጥሎ በሩን ሣይዘጋው ወጣ” አይናቸው ደም እንደጎረሰ ተከተሉት ፡፡ ግን ወጣትነታቸውን እሱ ውስጥ ያዩት መሠላቸው በሱ እድሜ ቀርቶ አሁን ከአምስት ዓመት በፊት የነበራቸውን ብርታትና ጥንከሬያቸውን ሲያስቡት ለራሣቸውም ይገርማቸዋል፡፡ ቁመናቸው እንደሱው ዘለግ ያለ ሆኖ ወገባቸው ወደፊት የተለመጠ ነው፡፡ ለማንም ርህራሄ የላቸውም በተለይ ማንም ጥቅማቸውን የነካ ሲመስላቸው ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ወደኋላ አይሉም፡፡ ያ በአባታቸው ውርስ የተደራደረ ወንድማቸውን እንኳ የቤቴን ጠባቂ ሰራተኛዬን ቀሚስ ነክቷል ብለው በሃሰት ያላገቡ ሚስታቸውን አስመስክረዋታል፡፡ አሁንም ታዲያ የልጃቸው በቤታቸው ውስጥ መሮጥ አልተመቻቸውም፡፡ “ነገ አደርጋለሁ አባባ ነገ ነገ ነገ” ንግግሩ በጆሮአቸው አስተጋባ “እኔ እምለው” አሉ አጠገባቸው ያለ መስሏቸው ፡፡ “ አሁን ጊዜው የኔ ነው ብለህ ነው እክድሃለው ውርስ አገኛለሁ ብለህ ነው ድንቡሎ የለም ” በለሆሣስ ተናገሩ ድምፃቸውን የሰማቻቸው ሰራተኛ “ ቅዠት ጀመሮት እንዴ በሞትኩት” አለች እና እራሷን አሰበች ፡፡ አንድ ቀን እንደሚስት በአደባባይ ማእረግ ሣይሰጡኝ አሁን እርሶ ሲሞቱ ምን ሊኮን ይሆን አለች በውስጧ፡፡ “አ!” አሉ ዓይናቸውን በልጥጠው፡፡ “እንዴ ምን ነካዎት ከዚህ ቀደም ሲታዘዞት አይደለም የኖረው? ዛሬ ነው በራሱ ፈቃድ ልውጣ ብሎ የሄደው፡፡ ምነው በዚህ እድሜህ ከኛ ጋር ተቆራመድ ማለት ጡር አለው?” አለች የልቧን ሐሣብ ያወቁባት ስለመሰላት ይህን ተናግራ እየተመናቀረች ወደ ጓዳ ገባች፡፡ “አሃ! አንቺም አለሽበት? የማንን እንጀራ የምትበይና የምታበይው መሠለሽ? አድማ ምቺብኝ! አንቺማ ትሄጃለሽ፤ ትሮጫለሽ፤ ምን አለብሽ? ቆይ ግድ፤ የለም? ፏሊብኝ ምን ታደርጊ!ስስት ዓመት አይደል አልጋ ላይ ከቀረሁ” ንግግራቸውን አቋርጠው ግርግዳ ግርግዳውን ማየት ጀመሩ ከዚህ ቀደም ከልጃቸው ጋር የተነጋገሩት አእምሮአቸው ውስጥ ይመላለሣል “ስማ አንተ ስጋውን ሣትነካ አሣምረህ እና አስተካክለህ ቁረጥ ዋ” አሉ “እንዳልከኝ አይደል የቆረጥኩት ምን አደረኩ” “በል ሞልጨህ እጠበኝ ምን ያጣድፍሃል እኔ እዚህ ቁጭ ብዬ ምን ልትሆን አማረህ ክንዴን ሣልንተራስ” “እንዴ አባባ ያልከኝን ሁሉ አደርጋለሁ ከዚህ በላይ ምን ልሁን “ “ወዲህና ወዲያ ማለት የለም ስርዓትህን ጠብቅ ህጌን አክብረህ ኑር ያለበለዚያ ለኔ ይሰንፋል ብለህ አታልም አገላብጥሃለው ዱላ ማንንም ይገዛል” ያለፉት ንግግሮቻቸው ብልጭ ድርግም እያለ አይምሮአቸው ውስጥ ይመላለስ ጀምሯል፡፡ ለሣቸው ብቻ በሚገባ ድምፅ መለፍለፍ ጀመሩ፡፡ እንደመሣቅ እያሉ እጃቸውን ዘረጉና አየሩን አቀፉት ልጃቸውን የሆኑ ያከሉ መሠላቸው፡፡ የለበሱትን ጂንስ ሱሪ አስተካክለው ጃኬታቸውን እየሠበሠቡ ባጠገባቸው የምታልፍ ቆንጆን ለመያዝ እጃቸውን ሲዘረጉ ሠራተኛውን እጅዋን ያዟት፡፡ “በስመአብ በስመአብ ምን ሆኑ አንቱ!” አለች እጃቸውን እየደባበሰች፡፡ እንደገና ፊታቸውን ቅጭም አደረጉና ማጉተምተም ጀመሩ፡፡ አፋቸው አልላቀቅ ሲላቸው ሰውነታቸውን አስተካክለው በጀርባቸው ተኙ፡፡ ሠራተኛቸው አለባብሣቸው እየተርበተበተች ወደጓዳ ገባች፡፡ የአቶ አስናቀ ፊት ሙልት ብሎ የጎልማሣነት ጊዜያቸው ላይ ያሉ መሠሉ፡፡ አፋቸውን ለመክፈት ይሞክሩና ያቅታቸዋል፡፡ እጃቸውን ለማንሣት ይታገላሉ ፡፡ በጉርምስና ጊዜያቸው የሚወዱትን እጀጉርድ ሸሚዝ የለበሱ ይመስላቸዋል ፡ ፡ ፈገግ ለማለት ሲሞክሩ ፈገግታቸው ይጠፋና እሚያስፈራ ድምፅ በጆሮአቸው ያስተጋባል፡፡ አይናቸው ክድን ግልጥ እያደረጉ እንደህፃን ልጅ ሲመላልሱ ቆይተው እንደደከመው ሰው በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ ከብዙ ቆይታ በኋላ ልጃቸው እናቱን አስከትሎ ገባ፡፡ “አባባ አባባ መጥቻለሁ” አለ እጁን ኪሱ እንደከተተ ዘና ፈገግ ብሎ ቁልቁል ከተጋደሙበት እያያቸው “እንግዲህ ኩርፊያውን ተውትና የሚፈልጉትን ይንገሩት” አለች አሰለፈች “አባባ ምን ነበር ያልከኝ” አለ አንገቱን ወደፊታቸው አስጠግቶ” አቶ አስናቀ አይናቸውን ኮርኒሱ ላይ እንደሰኩት አልተነቃነቁም፡፡ መለስ ብሎ እናቱን አያት “ምን ጉድ መጣብን አንተው ዛሬማ አንተ ከሄድክ ጀምሮ ተለዋውጠዋል፡፡ ፈርቼ ነበር የዋልኩት፡፡” “ምን አድርጊ ብሎ ነው?” “እኔንስ ምንም አላሉኝም፡፡ ግን ፈልገውህ ነበር፡፡ ይቃዣሉ፡፡” “አሁን ምን እናድርግ?” “ትንሽ እንጠብቃቸው፡፡ እራሳቸው ይንቁ፡፡” “ሌላ ጊዜ አያስችላቸውም፡፡ በስድብ አልነበር የሚቀበሉኝ?” “እስኪ ዞር በል፡፡” አለች ወደ ሽማግሌው እየተጠጋች፡፡ ከንፈራቸው ደርቋል፡፡ እጃቸው ቆርፍዷል፡፡ ደነገጠች፡፡ ትንፋሻቸውን አዳመጠች፡፡ “ምን ብዬ ላለቅስ ነው? አሠሪየ . . ምን የልጄ አባት . . . ባሌ. . . ምን ብዬ . . .” በፍጥነት ራሷን ጠየቀች፡፡ እጇ እየተንቀጠቀጠ የዓይናቸውን ቆብ ወደ ታች ገጠመችውና ልጇን እጁን ይዛ እየወዘወዘች “እትዬ ተዋበችን ቶሎ ጥራ!” “ለምን?” “በቃ! ሁሉም አልቋል!” “ምን! እማ ምን አልሽ?” አለ እየተርበተበተ፡፡ “ጉድ! ጉድ! ጉድ! . . . እያለች መጮኽ ጀመረች፡፡ ልጇም ተከትሏት ጮኸ፤ “አባባ . . . ደግ አባት እንዳማረኝ፤ አባባ! እጄን ይዘኸኝ ሳትሄድ . . . አባባ . . . አባባ!” እየጮኸ ማልቀስ ጀመረ፡፡ ከሰፊው ሳሎን ውስጥ የሁለቱም ድምፅ በየተራ መልሶ በጆሮአቸው ያስተጋባል፡፡
test