የሹመት ነገር ሲነሳ...ጌትነት ገሠሠ ይግዛው
Edited by : addiskignit@gmail.com -1/25/2023
ወዳጄ አፓርታይድ ቦቃ የለውም። በሚተናነቅህ ቋንቋ የዘር መድሎ ስርአት ማለት ነው ። ስለዚህ ስሙ ሲጠራ አይጎፍንንህ። ለአመታት እየኖርክበት ነው። ዘረኝነትን እያሞካሸህ፣ ከቱርፋቱ እፍታውን እየላስክ በስሙ አትጥሩኝ ማለት ውለታ ቢስነት ነው።ታስታውስ እንደሁ በአለም ላይ የመጨረሻው የአፓርታይድ ስርአት ከደቡብ አፍሪካ ከመወገዱ በፊት ይፋዊ መጠሪያው ይኸው ነበር። እርግጥ ነው የደቡብ አፍሪካ የዘር መድሎ ስርአት ሰለባዎች ስርአቱን አምርረው ይታገሉ ነበር። የእኛ ለየት የሚለው ጭቆናውን አምነን፣ አሚን አሚን ብለን፤ ጨቋኞቻችንን በጀርባችን አዝለን "ንጉስ ሆይ ሺ አመት ይንገሱ"ን እየዘመርን፣ ሲገፉን አሚን፣ ሲገሉን ይሁን እያልን ስርአቱን ለማጽናት ከገዥዎቻችን በላይ የምንተጋ በመሆናችን ነው። ያዝልቅልን እንጅ በዚህ አያያዛችን ባርነትን ተላምዶ በመኖር በአለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ መስፈራችን አይቀርም። በአፓርታይድ ስርአት ውስጥ የዜጎች መብት ዋነኛ መስፈሪያ ከገዥው መደብ ጋር ያላቸው የጎሳ፣የዘር፣የቀለም...ትስስር ነው። በመሆኑም እውቀት፣ስልጣን፣ኃላፊነት፣እድሜ ...ከዘር ማንነት ጎን ሲቆሙ እርባና ማጣታቸው እሙን ነው። ይህንን የዛሬው ኦህዴድ መራሹ የአፓርታይድ ስርአት ከማጎንቀሉ በፊትም ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት ኑረነዋል።ባይገባንም፣ባይመረንም፣ባያንገሸግሸንም የህይወታችን ታሪክ አካል ሆኗል። ስለዚህ ካንተ ጎሳ እንቶኔ ስለተሾመ ድቤህን አትደልቅ። በዚህ ሹመት ሆዱን ይሞላበታል እንጅ አያዝበትም። በእርግጥ አስፈላጊ ሲሆን የጌቶቹን ገመና እና ነውር ለመሸፈን ጭዳ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አልፎ ግን ከስርአቱ ባለቤት ፍላጎት ውጭ ጥቅሜን ያስጠብቅልኛል፣መብቴን ያስከብርልኛል ብለህ ተስፋ ካደረግክ ጉም ለመዝገን የሞከርከው አንተ ነህ ። ለማንኛውም ይህን ከላይ ለመግለፅ የሞከርኩትን ሀሳቤን በአንድ ምሳሌ ላሳይህ፣ ጠጅ በብርሌ ነገር በምሳሌ እንዲሉ አበው የጉምሩኩን ጉልበተኛ ላስተዋውቅህ። ፠ ፠ ፠ ፠ የጉምሩኩ ጉልበተኛ (ያለማስታወሻ የተጻፈ ማስታወሻ) ዘመኑ ሩቅ ነው። ያኔ ጫላ እንደኛ ህዝብ ነበረ። በአንጻሩ ገረስላሴ ሁሉ በእጁ፣ ሁሉ በደጁ ሆኖ ሲያሻው ይፈልጥ ሲያሻው ይቆርጥ ነበር።በእርግጥም ይህ ጊዜ ለገረስላሴ በስሙ ብቻ የሚፈራበት፣ የሚከብርበት፣ ያሻውን የሚረግጥበትና የሚደፍቅበት ነበር።ይህን ያነሳሁት የምነግርህ ታሪክ የሩቅ ዘመን መሆኑን እንድትይዝልኝ ብቻ ነው። ከእለታት በአንዱ ቀን የዕለታዊ ጋዜጣን ሆድ ለመሙላት አቀርቅሬ ባለሁበት ሰአት ነው ባለጉዳየ ቢሮየ ድረስ የመጣው። ምንም እንኳን ለነገው ጋዜጣ የሚሆን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ ቢሆንም አቋርጨ ማናገር ነበረብኝ። ነገሩ እንዲህ ነው። ባለጉዳዬ ኗሪነቱ ከአረብ ሀገራት በአንዱ ነው። ቤተሰቦቹ ደግሞ አዲስ አበባ ነው የሚኖሩት። ሰሞኑን የአመት እረፍቱን ወስዶ ከባለቤቱ እና ከልጆቹ ጋር ለማሳለፍ፣ ከዚያም አልፎ ወዳጅ ዘመዶቹን ለመጠየቅ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍሮ ቦሌ አየር ማረፊያ ይደርሳል። ከዚያም አስፈላጊውን የኢሚግሬሽን መስፈርት አሟልቶ፣ የያዛቸው ሻንጣዎች የጉምሩክ ፍተሻን እስኪያልፉ በመጠባበቅ ላይ እያለ የያዘው ሻንጣ እንደማይለቀቅለት ይነገረዋል። ቤተሰቦቹን ለማግኘት ልቡ ቢሰቀልም፣ ከመንገዱ የሚያስተጓጉለው ነገር በመፈጠሩ ብስጭት ቢገባውም እንደምንም ተረጋግቶ ለምን ብሎ ይጠይቃል። "ኮንትሮባንድ ነው አያልፍም!" ይለዋል ፈታሹ የጉምሩክ ሰራተኛ። አይደለም ብሎ ይከራከራል። "ለልጆቼና ለባለቤቴ የገዛኋቸውን ልብሶች እንዴት ኮንትሮባንድ ነው ትሉኛላችሁ? ነጋዴ አይደለሁም፣ በዚያ ላይ የያዝኩትም ልብስ ብዙ አይደለም "በማለት ሊያስረዳ ቢሞክርም የሚያዳምጠው አላገኘም።አጠቃላይ ሁኔታውን ሲያየውም መፍትሔ የሚያገኝ አልመስልህ አለው። በዚያ ላይ ቤተሰቦቹ በናፍቆት ይጠብቁታል። ግራ ገባው። በመጨረሻም "እሺ! ቢያንስ ለመውሰዳችሁ ደረሰኝ ስጡኝ" ይላቸዋል። ጉምሩኮች በዚህ ጥያቄውም የተደሰቱ አይመስልም። እሺም እምቢም ሳይሉ ብዙ አጉላሉት።ጠብቆ ጠብቆ መጨረሻ ላይ ትዕግስቱ አለቀና አምር ሮ ተናገረ።" ዘረፋ ከሆነ ንገሩኝ እንዴት ደረሰኝ ትከለክሉኛላችሁ?" ብሎ በመጮህ የብዙዎችን ትኩረት ሳበ። ይህም ሻንጣውን ባይሆንም ደረሰኝ ለማግኘት ረዳው። ደረሰኙን ይዞ ለሰአታት ሲጠብቁት ከነበሩት ቤተሰቦቹ ጋር ተቀላቀለ። የሆነበትን ነገር ባለማሰብ የቤተሰቦቹን ናፍቆት ለመወጣት ጥረት ቢያደርግም ስሜቱ መደፍረሱን መደበቅ አልቻለም። በተለይ ህጻናት ልጆቹ ምን እንዳመጣላቸው ሲጠይቁት ይበልጥ ጥቃት ተሰማው። በማግስቱ በጧት ወደ ቦሌ ጉምሩክ ቢሮ በማምራት "አላግባብ፣ አለ ህግ ለቤተሰቦቸ ያመጣሁት ልብስ ተወርሶብኛልና ይመለስልኝ" ሲል ለስራ አስኪያጁ አመለከተ። ስራ አስኪያጁ አቶ ዘይኑ አቤቱታውንና ብሶቱን በትዕግስት አዳመጡት። ከዚያም በደረሰበት መጉላላት ማዘናቸውን ገልፀው የተወረሰውን ንብረት በተመለከተ ውሳኔ መስጠት እንዲችሉ ማመልከቻውን በፅሁፍ እንዲያቀርብ ጠየቁት። እዚያው በተቀመጠበት ማመልከቻውን እንዲጽፍም እስክርቢቶና ወረቀት ሰጡት። ጽፎ እንዳጠናቀቀም እዚያው እፊቱ መሰል ጉዳዮችን አይቶ የውሳኔ ሀሳብ ለሚያቀርበው ኮሚቴ መሩት። ባለጉዳየ በስራ አስኪያጁ ቀናነት ትናንት የተሰማው ምሬት ሲሽር ታወቀው። ንብረቱ ባይመለስለትም በአግባቡ ብሶቱን ስላዳመጡት፣ጉዳዪንም በተገቢው መንገድ እንዲታይለት ስለመሩለት በእፎይታ ወደ ቤቱ አመራ። ባለጉዳየ የእረፍት ጊዜውን ለማሳለፍ ወደ ሀገሩ ሲመጣ ለደቂቃም ቢሆን ከቤተሰቦቹ የመለየት ሀሳብ አልነበረውም። አሁን ግን ባለጉዳይ ሆኗል።እናም በጧት ተነስቶ ወደ ቦሌ ጉምሩክ አምርቷል። እዚያም እንደደረሰ ማመልከቻውን ወደተቀበሉት ስራ አስኪያጅ ቢሮ አመራ ። ጉዳዩ የተመራለት ኮሚቴ የተያዘው ንብረት በጉምሩክ ከተፈቀደው የዋጋ ግምት በታች በመሆኑ መያዙ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ለባለ ንብረቱ እንዲመለስ የሚል የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል። ስራ አስኪያጁ አቶ ዘይኑም የውሳኔ ሀሳቡን አጽድቀው የተያዘው ንብረት ለባለቤቱ እንዲመለስ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ባለጉዳየ ይህ ሲገለጽለት እጅግ መደሰቱን በመግለጽ ለስራአስኪያጁ ምስጋና አቀረበ። ስራ አስኪያጁ በበኩላቸው ዕቃው መጀመሪያም መያዝ ያልነበረበት መሆኑን ከኮሚቴው መረዳታቸውን በመግለጽ ለሆነው ነገር ሁሉ ይቅርታ ጠየቁት።በስራ አስኪያጁ ትህትና እየተደነቀ፣ ለሁሉም ሹም አለው የሚለውን ብሂል እያሰበ ንብረቱን ለመረከብ ወደ ግምጃ ቤት አመራ ። እዚያም እንደደረሰ የስራ አስኪያጁን ውሳኔ የያዘውን ደብዳቤ በማሳየት ንብረቱን ተረከበ። አሁን ቀሪው ነገር እቤቱ ደርሶ የህጻናት ልጆቹን ደስታ ማየት ነው። ይህን በአይነ ህሊናው እያሰበ ንብረቱን ተሸክሞ ከጉምሩክ ግቢ ለመውጣት ጉዞ ጀመረ። የጉምሩክን ግቢ ከመልቀቁ በፊት ግን በር ላይ ለመፈተሽ መቆም ነበረበት። ይህ ፍተሻ የጉምሩክ ፍተሻ አይደለም። የተለመደው ከየትኛውም መስሪያ ቤት ሲወጡ የሚደረግ ፍተሻ በመሆኑ ብዙም አላሳሰበውም። የያዘውን ንብረት ይዞ እንዲወጣ የተፈቀደበትን ደብዳቤ ለጥበቃ ሰራተኛው ሳይጠየቅ ሰጠ። ከዚያ ግቢ ቶሎ ለመውጣት ቸኩሏል።እሱ በአካል እዚያው ቢሆንም በሀሳቡ እቤቱ ደርሷል። የጥበቃ ሰራተኛው በበኩሉ ዘና ብሎ ሻንጣውን ይበረብራል። እያንዳንዱን ልብስ ከሻንጣው እያወጣ እያራገፈ ወለሉ ላይ ይጥላል። እንደገና መልሶ ከወለሉ ላይ እያነሳ ወደ ሻንጣው ይወረውራል። ባለጉዳይ በሁኔታው ግራ ሲገባው "ደብዳቤውን አይተኸዋል?" ብሎ ጠየቀ። ጥበቃው ገረስላሴ ለተጠየቀው ምላሽ ሳይሰጥ እንደ አዲስ ደብዳቤውን አገላብጦ ማየት ጀመረ። በመቀጠልም አዲስ ሀሳብ እንደተከሰተለት "መታወቂያ አለህ?" ሲል በቁጣ ድምፅ ጠየቀ። ባለጉዳየም ፍተሻው እንደተጠናቀቀ በማመን መታወቂያ ስላልነበረው ፓስፖርቱን ሰጠ። ባለጉዳይ ንብረቱን ተረክቦ ከዚያ ግቢ ለመውጣት ቸኩሏል። ጥበቃው ገረስላሴ በአንጻሩ ጊዜ ሞልቶ እንደተረፈው ያስታውቃል። ፓስፖርቱን ያገላብጣል፣ ከስራ አስኪያጁ የተጻፈውን ደብዳቤ እንደ አዲስ እያነሳ ይጥላል። በዚህ ሁኔታ ብዙ ደቂቃዎች አለፉ። ከብዙ ጥበቃ በኋላም ጥበቃው ገረስላሴ ንብረቱን እንደማይመልስ አሳወቀ። ባለጉዳይም ለምን? ብሎ ጠየቀ። የረባ መልስ ሳይሰጠው ከጥበቃ ቢሮው እንዲወጣ ጠየቀው። ምርጫ አልነበረውም መሳሪያ ከታጠቀ ሰው ጋር ሀይለ ቃል መነጋገርም ሆነ መጨቃጨቅ እንደማያዋጣው በማመን ፓስፖርቱን ተቀብሎ ለመሄድ ወሰነ። ይህም ግን አልተሳካለትም። ገረስላሴ ፓስፖርቱንም አልመልስም አለ። ምርጫ አልነበረውም ተመልሶ ለስራ አስኪያጁ አቤት አለ። ጭራሹንም በር ላይ ፓስፖርቱን እንደተነጠቀ ገለጸ። ስራ አስኪያጁ ተበሳጬ፣ ለሌላ የድርጅቱ ሀላፊ ደውለው ባስቸኳይ ንብረቱንና ፓስፖርቱን ተረክበው እንዲያመጡ አዘዙ። ብዙ ደቂቃዎች አለፉ። የሚጠበቀው ንብረት ግን ሊመጣ አልቻለም። ደጋግመው ስልክ መቱ በዚህም ገረስላሴ በእምቢታው መጽናቱን አረጋገጡ። ምርጫ አልነበራቸውም ባለጉዳዩን ቢሮአቸው ትተው እራሳቸው ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጡ ሄዱ። አልተሳካላቸውም። ገረስላሴ "አንተ አታዘኝም !"አላቸው። በስራ አስኪያጅነት የሚመሩት መስሪያ ቤት የጥበቃ ሰራተኛ በሌሎች የድርጅቱ ሰራተኞች ፊት አመናጭቆና አቃሎ መለሳቸው። የቦሌ ጉምሩክ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዘይኑ የጥበቃ ሰራተኛውን እብሪት እና ንቀት ዋጥ ከማድረግ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። በደብዳቤ ከማዘዝ አልፈው በስራ ኃላፊዎች አስጠይቀውታል፣ ይህም ሳይሳካ ሲቀር እራሳቸው በአካል አነጋግረውታል። ይህን ከማድረግ ሌላ ቡጢ አይገጥሙ ነገር፣ ለነገሩ በእሱም ቢሆን አሳዛኝ ተሸናፊ እንደሚሆኑ አላጡትም።ሰውየው ገረስላሴ ነው፣ከዚያም አልፎ ባለጠመንጃ። ግራ ገባቸው፣ የባለጉዳዩን ፊት ማየትም አሳቀቃቸው።ግን ምርጫ አልነበራቸውም ቢሮአቸው ቁጭ ብሎ እየጠበቃቸው ነው። የባለጉዳየ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ። ጉምሩክ ያለ አግባብ የወሰደበትን ንብረት ለማስለቀቅ ሄዶ የጉዞ ሰነዱን ፣ፓስፖርቱን ተነጠቀ። "እሺ ንብረቱ ይቅር ፓስፖርቴን መልሱልኝ "ቢልም ሊሳካለት አልቻለም። "ጉድ ነው!" እያለ፣ በመጠቃቱ እያጨበጨበ የስራ አስኪያጁን ስልክ ሊጠብቅ ተስማምቶ ወደ ቤቱ አመራ። ቀናት አለፉ፣ አቶ ዘይኑ ግን የጉምሩኩን ጉልበተኛ በአለቃነት አስገድደው፣ በስራ ባልደረባነት አባብለው እና መክረው ያላግባብ የወረሰውን የግለሰብ ፓስፖርት እና ንብረት ማስመለስ አልቻሉም። ይህ ጉዳይ እኔ ጋር የደረሰው እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው። አቶ ዘይኑ ጋር ደወልኩ፣ በዚህም የታሪኩን እውነተኝነት አረጋገጥኩ። በቃለ ምልልስም ይህ ሁሉ ሲሆን በኃላፊነታቸው ለምን አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ እንዳልቻሉ ጠየቅኳቸው። መልሳቸው ግልጽ አልነበረም። እንደተቸገሩ ያስታውቃል። የባለጉዳዩን አቤቱታ፣ የስራ አስኪያጁን ምላሽ እና አስፈላጊ የሰነድ ማስረጃዎችን አካትተን ታሪኩን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አወጣነው። ጉዳዩ ፓስፖርት ለሚሰጠው ለኢሚግሬሽንና ዜግነት ዋና መምሪያ(ትክክለኛ ስሙ ላይሆን ይችላል) በመድረሱም መምሪያው ለጉምሩክ ደብዳቤ ጻፈ። ማንም ፓስፖርት የመቀማትም ሆነ የመውረስ መብት የሌለው መሆኑን በመግለጽ በአስቸኳይ ለባለቤቱ እንዲመልሱ፣ ይህንንም ድርጊት በፈፀመው ሰራተኛ ላይ እርምጃ ወስደው እንዲያሳውቁ ደብዳቤ ጻፈ። ይህንንም ከተጨማሪ የኃላፊዎች ማብራሪያ ጋር አተምነው። ታሪኩ ሲወጣ ጉምሩክ ተተራመሰ። በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ስርአት አልበኝነት መስፈኑ መነጋገሪያ ሆነ።ይህ ሁሉ ሲሆን ሳምንት እየጠበቅን የምናወጣውን ታሪክ እያነበቡ ጉድ ከማለት ውጭ በገረስላሴ ላይ የተወሰደ እርምጃ አልነበረም። ከእለታት በአንዱ ቀን ግን አቶ ዘይኑ መጨከናቸውን የሚያሳይ ደብዳቤ ከመዝገብ ቤት ወጣ።እኔም በዚያው ቀን ከጧቱ ሶሰት ሰአት ላይ የደብዳቤው ኮፒ ደረሰኝ። ገረስላሴ ከስራ መታገዱን የሚገልጽ ነበር። ወዲያው ለአቶ ዘይኑ ደወልኩና በመጨረሻ እርምጃ ወሰዳችሁ አሉ አልኳቸው። "የምን እርምጃ?" አሉኝ። የቅጣት ደብዳቤ መጻፉን መስማቴን ገለጽኩ ። አስተባበሉ። "ውሸት ነው" አሉኝ። ከፊቴ ያለውን ደብዳቤ እያየሁ የሆነ ነገር እንደተፈጠረ ጠረጠርኩ። ስልኩን ከዘጋሁ በኃላ ሁኔታውን ለማጣራት ጉምሩክ ደወልኩ። አቶ ዘይኑ ገረስላሴን ከስራ ማገዳቸውን፣ ወዲያው ግን ደብዳቤውን እንዲሰበስቡ ከበላይ አለቆቻቸው መታዘዛቸውን እና ደብዳቤውም መሰብሰቡን አረጋገጥኩ። አቶ ዘይኑ ደብዳቤው በዚያ ፍጥነት ከእኔ እጅ ይገባል ብለው አለማሰባቸው ገባኝ።አሳዘኑኝ። ይህም ሆኖ ታሪኩን ከነተሰበሰበው ደብዳቤ አተምነው። የጉምሩኩን ጉልበተኛ ከነ ጉልበቱ ምንጭ ለአንባቢ አጋራነው። ገረስላሴ የትግራይ ተወላጅ ነው፣ ገረስላሴ የህወሀት አባል ነው። አቶ ዘይኑን ጉልበት የነሳቸው እኛን ምንዱባኖቹን መሆናቸው ነው። የሹም ሽር ነገር ሲነሳ ይሄ ታሪክ ትዝ ቢለኝ አትፍረዱብኝ። ያገሬ ሰው " የማይተኮስ ጠመንጃ ከዱላ ቁጥር ነው" ያለው መቸም ወዶ አይደለም። እኛ ግን ለዛሬው ባለጊዜ ጫላም "ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች" ን እየተረትን አለን፣ ለጉድ የፈጠረን።
test