የልቤ ቅርፊት/አጭር ልብወለድ-/ሶስና አሸናፊ/
Edited by : Gezahegn Mekonnen Demissie -10/11/2025

ከአደረገችው የክር  ኮፍያ ስር ሾልኮ የወጣ ነጭ ፀጉሯን አተኩሬ ካለይሉኝታ አየሁባት። ሽበቷ የእድሜ ሳይሆን የኑሮዋ አሳባቂ ነው። ሰው አይታ የምታውቅ የማትመስለው ይህቺ ሴት ወዟ ሳይቀር ገርጥቷል ። ተጠግታ ከጀርባዬ ከተደረደሩት አሮጌ እቃዎች መሀል ካሜራ ጠየቀችኝ። ደነገጥኩ። የደነገጥኩት ቃሉ ከአፏ ሲወጣ ደረቅ ቀይ ከንፈሯ በስሱ በመሠንጠቁ ነው። አፏ ተንቀሳቅሶ የሚያውቅ አይመሥልም ። ለጠባብ አፏ ምራቄን ማዋስ አማረኝ። 

እሷ ግን የደማ ከንፈሯን በምላሷ እየላሠች የተበጠሰ ሀብል ከቀይ ያረጀ የቆዳ ቦርሳዋ ውስጥ አውጥታ ከሰጠኋት ካሜራ ጋር አወዳደረችና ለራሷ የሆነ ነገር አጉተመተመች። ቦርሳው አርጅቷል። ልብሷ የጡቷን ጫፍ መቆም አጋልጦ ያሳያል። የስሜቷ ወላፈን ገረፈኝ።ደግሜ ደነገጥኩ። የጡቷ ጫፍ አይኔን ወጋኝ ሰውነቴ በሙቀት ተቀጣጠለ። አይኔንም ከጡቷ ጫፍ ላይ አልነቀልኩም። ጡቷ ጫፉ ቡኒ ነው። 

ተጋልጣ ስላጋለጠችኝ አፈርኩ

በእፍረቴ ተሸሽጌ ሚስቴን ይቅርታ ጠየኳት።

ሚስቴ የልቤ ቅርፊት ናት። እኔና እሷ ትላንት ማታ  እግሮቻችን ተቆላልፈው ስንቃትት ለሊቱ ነግቷል። ሰውነታችን እንደጥጥ እየተባዘተ ሲወድቅ የደስታችን ተራራ ውስጥ ገብተን ተመሸገናል።. አላልቅ ያለ የሀሴት ክምራችንን እንደሁል ጊዜ ስንቦጠቡጠው አድረናል። እንደ ዘወትሩ እንደ ትኩስ ቀረፋ የሚጣፍጥ ትንፋሽዋን ስምግ ፣ አቅፌያት የስሜቷ ወላፈን ጉልበቴን ሲያብረከርከው ፍቅሯ እንደመላእክት ክንፍ እንደሁሌው ሲያቅፈኝ ትላንት ሌሊት፤  ዛሬ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ  የማላቃት ሴት ስሜት እንደከርቤ ጢስ አጠነኝ።

ይህቺ ሴት ዘመናዊ ሴት እንደነበረች ገፅታዋ ይናገራል።

"እኔ መዋሸት አልፈልግም ብዙ መጠጣቴን ጭምር ልነግርህ እፈልጋለሁ። ማንነቴ በጥቀርሻ እንደተሸፈነ ቤትና እንዳረጀ እቃ እንዲሆን አልፈልግም። " አለች።

እውነቷን መሠለኝ። ታሳሳለችም ሁለመናዋ የነተበ ይመስል ደግሞ ታሳስባለች። የተዘጋ ቤት ጠረን አላት ። 

"አየኸው? " አለች ከሌሎቹ ደንበኞቼ ድምጿን ከፍ አድርጋ።

መልስ ሳልሰጣት በፀጥታ አተኩሬ አየኋት ። በእድሜ አልገፋችም ግን ሰውነቷ ከፀሀይ እርቆ ቢሠነብትም ለመታየት ይገዳደራል። 

 ካሜራውን በመሥጠትና ባለመሥጠት መሀከል ሆና ለራሷ የሚገባትን ነገር ተናገረች።

"እርዳኝ" አለችኝ አይኗን ሰብራ።  

የእኔ ልብ ግን ፈርቷታል።

"ካሜራው ያስፈልገኛል።" አለች በማንሾካሿክ አይነት።

.ደግማ ለብቻዋ አጉተመተመች እና ወደአፏ እንድጠጋ ምልክት ሰጠችኝ።

በሰማያዊ አይኗ ውስጥ ገብቼ ውስጧን ለማንበብ ስሞክር ትንፋሿ ፈጀኝ።

ካሜራውን ስሰጣት እጄን ያዘችኝ። እጇ ለስላሳ ቢሆንም የሚቧጥጥ ነገር አለው።ደስ የሚል ቡጥጫ ነው። መቧጠጡ ለሠውነቴ የተለየ ስሜት ነበረው። ሳላስበው በተራዬ ተጫንኩት እጇን።

"ምን ፈልጌ መሠለህ?" አለች ሀብሏ ላይ እንዳቀረቀረች 

"ምን?" አልኳት እጄን ከእጇ ለማላቀቅ እየታገልኩ።

"አግዘኝ ካሜራ ያስፈልገኛል። ሀብሉን አላደርገውም። ሀብሉ የውዱ ስጦታዬ ነው። ካለ እሱ ምን ያደርግልኛል።

ተቀበልኳት እና እሷ እንዳደረገችው ጫፍና ጫፉን ይዤ አጥመዘመዝኩት። ውዴ ያለችው ሰው ምን እንደሚመስል ለማሠብ። እቃ በእቃ እንደማንለውጥ ላስረዳት ሞከርኩ። አብረዋት የቆሙ ደንበኞችም ሊያስረዷት ሞከሩ። በሌሎቹ ፊት ግርግር መፍጠር አልፈለኩም ግን ለምን ካሜራ መግዛት እንደፈለገች ልጠይቃት ሳቅማማ ቀድማኝ

"የለኝም ታውቃለህ ብትረዳኝ ደስታዬ ነው" አለች እና አካባቢዋን ቃኘች።ግን ደግሞ አካባቢዋ የሚያስጨንቃት እንዳልሆነ ትከሻዋን ሰበቀች። በዚህ መሀል ሀብሉ ከእጄ አምልጦ በእሷ በኩል ወለሉ ላይ ወደቀ። አይኗን ጎልጉላ አየችኝ። ከምኔው እንደተከፋች ሳላውቅ እንባዋን ዘረገፈችው። ከመደርደሪያው ወጥቼ ሀብሉን ከመሬት ለማንሳት ብፈልግም መራመድ አቃተኝ።

"ምን ማድረግ አለብኝ?" አለችኝ ሀብሉን በቅልጥፍና አንስታ ወደእኔ እየተመለከተች። 

" ካለደረሰኝ መሥራት አልችልም። ያልተገዛ እቃ አንለውጥም " አልኳት እንድትሄድ በማሠብ።

" ገብቶሀል ? አባቴም እናቴም ሞተዋል ብቸኛ ነኝ። ማድረግ የምችለውን ሳላደርግ ነው ያደኩት እናቴና አባቴ በመለያየታቸው። ንግግሯን አቋርጣ ማሰቧን ቀጠለች።

"ምሽትን አልወደውም" አለች ውጭውን እያየች።

መምሸቱን እንኳ አላስተዋልኩም ነበር። 


ሌሎች ደንበኞች እንዳይገቡ በሩን መዝጋት ስለነበረብኝ ባለችበት ጥያት ወደበሩ አመራሁ። የጉስቁልናዋ ብርሀን ቤቱን የሞላው መሠለኝ። በደንብ አየኋት እሷም ማጉተምተሟን ትታ አየችኝ። እየተቁነጠነጥኩ ጠበኳት። በምላሷ ከንፈሯን መጠራረግ ጀመረች። የሰውነቴን ክህደት እያሸተትኩኝ መሥኮት ልዘጋ ተራመድኩ  ግን ደግሞ አይኔን ከሰውነቷ ላይ መንቀል አቃተኝ ተመልሼ ታክኬያት እንደቆምኩ በሩ ተከፈተ። 

"ብደውል ስልክህን አታነሳም በሰላም?" አለችኝ ሚስቴ።

ከገባሁበት ድንጋጤ መውጣት አቃተኝ እና አየኋት።

"ካሜራ ፈልጌ ነው። ታውቂያለሽ ሁሉ ነገር ተከልክያለሁ። አሁን ያለሁት ብቻዬን ነኝ ። የሰው ረሀብተኛ ነኝ። ገፄን ተነጠኩ። በግፈኞች ምስሌ ጠፋብኝ . . . ብዙ የሆንኩ ነኝ እኮ! " ክሩ የለቀቀ ሻርቧን ከትከሻዋ አውርዳ መደርደሪያው ላይ አስቀመጠች።

ሚስቴ አየችኝ በመደናገር አየኋትና አንገቴን ወደ ሴትየዋ መለስኩት።

"ዛሬ ደግሞ ምኗን ነው ያመጣብን" አለችኝ። በሱቁ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች ስለሚመጡ።

" ክርስቲና እባላለሁ" አለች እጇን ወደሚስቴ ዘርግታ

" ሮዛ እባላለሁ የኬቭን ባለቤት ነኝ" አለቻት

"ይገርምሻል. . ብቸኝነት ሲጠብሰኝ ቆልፈውብኝ ሲሄዱ የማወራው ከጭኔ ጋር ነው።አንቺም እንደኔ ከጭንሽ ጋር ትጫወቻለሽ?" ብላ ወገቧ ላይ የቋጠረችውን የቀሚሷን መቀነት ስትፈታው በጥፊ ይሁን በመቆንጠጫ የተንገበገበው ጭኗ ፊታችን ተጋለጠ። ሚስቴ ጮኸች የሆነ ልብ የሚነሳ ነገር ተሰማኝ። ቲማቲም የሚያካክል የቁስል ቅርፅ አርፎበታል። 

"አስበሽዋል እሱን ብለሽ ከሀገርሽ ወጥተሽ ማንንም በማታውቂበት ሀገር ማታ ፍቅርን ስትጋሪ አድረሽ ጠዋት የምትወጂውን ሰው ከጎንሽ ስታጪው? መጠጥሽን ሲነጥቁሽ አንቺ ደግሞ በማታውቂው ምክንያት በምታውቂያቸው ሰዎች በር ሲቆለፍብሽ? ምርጫሽ ጭንሽን መደብደብ ነው አይደል? " አለች አውልቃ የነበረውን ልብሷን አንጠልጥላ ለመውጣት እያቆበቆበች።

test