ብሊንከን አዲስ አበባ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እየተወያዩ ነዉ
Edited by : addiskignit@gmail.com -3/15/2023
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ። ትናንት ማክሰኞ ምሽት በዝናባማዋ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ጣብያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አቀባበል አድርገውላቸዋል። አንቶኒ ብሊንከን ዛሬ አብረዋቸዉ የመጡትን ልዑካኖች አስከትለዉ ከኢትዮጵያዉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር እየተነጋገሩ ነዉ። ብሊንከን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ብሎም ከአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ብሊንከን ዛሬ ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ራስ መኮንን አደራሽ በተዘጋጀዉ መድረክ ለጋዜጠኞች መግለጫ እንደሚሰጡ አዲስ አበባ የሚገኘዉ የአሜሪካ ኤንባሲ አስታዉቋል። የአሜሪካዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ ጉብኝት ዋንኛ ዓላማ የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነትን ለማስቆም የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ፕሪቶርያ ላይ የደረሱት የሰላም ስምምነት ተግባዋዊነትን መፈተሽ ብሎም በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረግ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ በሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት፤ በምግብ ዋስትና እና በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ከለጋሾች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ብሊንከን ከኢትዮጵያ በመለጠቅ ኒጀርን እንደሚጎበኙ የጉዞ መረሐ-ግብራቸዉ ያሳያል።
test