
በራሳቸው ስም ከሚምሉት አንዷ በመሆኔ መሥከሬን ለማቆም እና ገደብ የለሽ ጠጪነቴን ለመተው ሄለን ትሙት ስል በስሜ ምዬ ከስካር አለም ወጥቻለሁ።
ከመጠጥ አለም እራሴን ገፍቼ ለወጉ እንደዛሬው አንድ ወይ ሁለት ጎርደን ጅን በስትሮ ይዤ እቀመጣለሁ እንጂ እንደከዚህ ቀደሙ ከወንዶች እኩል ጠርሙስ አላወርድም። አለፈ ያ አስፈሪውና የህይወቴ ዝርክርክ ዘመን። ይሄ ማለት መጠጥ በደረሰበት አልደርስም ማለት ግን አይደለም። ሰው ማሽተት እፈልጋለሁ ሁካታ ውስጥ መሸሸግ እና ከብቸኝነቴ መጥፋት።ለዚህም በሰአቴ እዚህ ግሮሰሪ እገኛለሁ። አብረውኝ ያሉት የግሮሰሪው ደንበኞች ከሰላምታ በቀር ወሬአቸው አይመቸኝም። አድመኝነት እጠላለሁ። እዚህ ግሮሰሪ የሰው አይነት ይመጣል ግን በራሳቸው ልክ የሚያስቡ ሰዎች ደግሞ ጉራው ገደለን ብለው ሊያም የተባለውን የግሮሰሪውን ደንብኛ በገባና በወጣ ቁጥር እያነሱ ሲጥሉት አይቼ ሸሸኋቸው። እሱም ይህን ስለሚያውቅ . . . .
"አስመሳይነቴን ለማወቅ አብራችሁኝ ያላችሁትን ቆንጆዎች ማየት በቂዬ ነው።" ይላል በሟሽሟጠጥ
የግሮሰሪውን ታዳሚ በአይኑ እየገረመመ።
"ግን ዋናውና አሳሳቢው ነገር ለኔ ጓደኛ በመምሰል ወይም እኔ የተሻልኩ ነኝ በማለት ሌላውን አስጠይና አስወዳጅ መሆኔን እንደጀብዱ ባገኘሁት አጋጣሚ የየሰዉ አንገት ላይ ተንጠልጥዬ ለማሳየት አለመሞከሬ ነው። ሲል ዴቪድን እያየ ተናገረ ዛሬም።
"መፈላሠፍህ ባልሆነ " አለ ዴቪድ ቢራው ላይ አፍጦ።
ቤቱ ለደቂቃ በፀጥታ ተሞላ።
የቤቱን ፀጥታ በመታከክ ሊያም " አስቀያሚ እስተሳሰብ ወደውስጤ ማስገባት አለመቻሌ ልክ እንደእናንተ ወይም በመንጋ ከማሰብ መታቀቤ? ከፈሰሰው ሳልፈስ ከሮጠው ጋር ሳልሮጥ? ወሬ ተቀብዬ ሳላውቀው እንዳልጠላው በወሬ ብቻ በመተዛዘል" አለ ድምፁን አጉልቶ ወደ ግድግዳው ላይ በስእል ለተቀመጡት የጓደኛማቾች ምስል እጁን እያመለከተ። ወንበር ሳይዝ እንደመጣ ጮክ ብሎ መናገሩ ለአዲስ ደንበኞች ግርታ ቢፈጥርም ሌሎቹ ግን ስለለመዱት አጉረመረሙ።
ግሮሰሪው ሁሌም ከስራ በኋላ እንደተጨናነቀ ነው።
ወንበር ሲፈልግ አይን ለአይን ስለተገጣጠምን ወደኔ እንዲመጣ በአይኔ ምልክት ሰጠሁትና በቅልጥፍና ትንሿ ቦርሳዬን ከወንበሩ ላይ አንስቼ ጭኔ ላይ አስቀምጬ እንዲቀመጥ ጋበዝኩት።ሳያመነታ በግርታ ውስጥ ሆኖ አጠገቤ ተቀመጠ። ለመጀመሪያ ጊዜ ጎን ለጎን ተቀመጥን። ሊያም እኔ የምወደውና የምመርጠው አይነት ወንድ ባይሆንም ኩራቱን እና ሀቀኛነቱን እወድለታለሁ።
ስሙ ሊያም መሆኑን ያወኩት እነሱ እያነሱ ሲጥሉት በቅርብ ነው።
ሊያም ዘመናዊ እና ንግግሩ በእውቀት የተሞላ ነው።
በመካከለኛ ቁመቱ ውስጥ ኩሩነቱ ይታያል። እንደሚጠጣው ውስኪ አለባበሱም የዘነጠ ነው። ከዚህ ባሻገር እውቀቱን ለሌሎች ለማጋራት ወደኋላ አይልም። ከዴቪድ ጋር ጦርነቱም የእውቀት መሥሎኛል። እኔ እንደማየው እና እንደሠማሁት "ከማን በልጦ ነው ላስተምራችሁ የሚለው" ይለዋል ። የሁለቱ መጠጥ ልዩነት ቢራና ውስኪ ነው። ዴቪድ ሁሌ ቢራ በመጠጣቱ ይናደዳል።
"ወዳጆቼ እኔን የሚችለኝ ቤቴ እናንተን የሚችላችሁ ቤታችሁ እንደጨው በየቦታው ተበትነን እንኳን አለመተዛዘናችን ይገርማል ። የእኔ እንኳን እዳው ገብስ ነው ክፋቴን የማወርሰው ልጅ የለኝ ድስት የለኝ ። ግን ማን እንደሚያሳምፅብኝ አውቃለሁ።ይብላኝ እንጂ ለአደራ ተረካቢዎቹ እና ለታዳጊዎቹ እንደአሜባ መከፋፈላችንን ለምናወርሳቸው ወየው በሉ ልጅ ለወለዳችሁ " አለ
ማንን ሊናገር እንደፈለገ ገብቶኛል ግን ዛሬ አምርሮ ታየኝ። የሚጣላ ስለመሠለኝ እራሴን አዘጋጀሁ እሱን ለመከላከል። የእኔንም ጥላቻ ደርቦ የተናገረልኝ ስለመሠለኝ ግን ዴቪድን በአሽሙር ሲሰድብልኝ አንጀቴ ራሰ።
ባለጌ ወንበር ላይ ከዴቪድ ጎን የተቀመጡት ሊያምን ማሽሟጠጥ ጀመሩ።
"መቼም ሠምታችኋል ብዬ አስቤያለሁ። በአእምሮአችን ውስጥ ስላለው ጠቃሚ ነገር እየተቀባበልን ከመኖር ይልቅ አንዳችን ለሌላችን ልምጭ እንቆርጣለን። መባሉን?" ደግሞ እስከመቼ እየተገፋፋን ቁልቁል እንወርዳለን ብሎ የሚጠይቅም አልተገኘም አሉ። ዘንድሮ አሉ ነው ጉድ ያፈላው" አለ ። ሊያም እንደጉጉት አፍጠው ከሚያዩት ፊቱን ወደኔ መልሶ። ትከሻዬን ሰብቄ ዝም አልኩ።
ዴቪድና ሊያም በአንድ መሥሪያቤት እንሰራለን ከማለት ባሻገር አንድ ሰፈር አድገናል ሲሉ ሰምቻለሁ ወደፀብ ከማምራታቸው በፊት። ግን ሊያምን ሲያየው ደስተኛ እንዳልሆነ የሚታየው ዴቪድ ነው። ለዚያም የራሴ የሚላቸውን ሰዎች በሊያም ላይ አሳምጿል። አመፁን ደግሞ የቡናቤቱ ባለቤት በቅሬታ ሲያወራ ሰምቻለሁ። "ለወጣ ለገባው አይምሮው ተነክቷል በቅቶታል ከበፊትም ባይ ፖላር አለበት እያለ" ዴቪድ የሊያምን ስሙን ያጠፋል ።" ይላል ። ይህንን ከግሮሰሪው ባለቤት ስሰማ ደንግጫለሁ።ባለቤቱ ዴቪድን ታዝቦ ሲያወራ "ስም ማጥፋቱን ተክኖበታል። ሊያምን እንደተከታተልኩት ወሬ ከጀመረ የሚያወራለት ሰው የተረዳ እስኪመሥለው አያቋርጥም። ስለሚሠራው ስራ ዝርዝር ማስረዳት ወይም በእውቀት መናገር ይወዳል እንጂ ጉራው እንደሆነ እንጃ ! ሁለቱንም ያገኘኋቸው አንድ ላይ ነው ሊያም ባይፖላር አለበት ያለኝ ዴቪድ ብቻውን መጥቶ ነው።" ብሏል። ሊያም ግን የሰማውን ሰምቶ እንዳልሰማ ቢያልፍም በመጠጥ ቤቱ ውስጥ እጁን ኪሱ በመክተት እየተንጎራደደ ይናገራል። በዚህም ባለቤቱ ምንም አይለውም። ደግሞ እኔ እንዳየሁት ያምርበታል ።አጭር ሪዙን በእረጃጅም ቀጫጭን ጣቶቹ ይነካካታል።
እና ዛሬ ከእሱ ጋር ለመሠለፍ ተዘጋጅቻለሁ። ልጋብዝህ ለማለት ወደኋላ አልልም። ሰክሮ አይቼው አላውቅም። ግን እንስከር ቢለኝ እንኳን እስማማለሁ። አንዳንዴም ፍልስፍናውን ስለማይረዱት ራሳቸውን ለመሸፈን ያመዋል በሚል እሱ ላይ የደፈደፉት ባይ ነኝ። ሊያም ግን ጤነኛ ነው ብዬ በድፍረት ባልናገርም የህመምተኛ መልክ አይታይበትም። ዴቪድ ሲንጎራደድ ሲያየው ብስጭቱን መቆጣጠር ያቅተዋል ባይ ነኝ። እንደውም ችግር ያለበት ዴቪድ ነው። ከሁሉም ጋር ሰለም መሥሎ ለመታየት ከመፈለጉ የተነሳም የተጣሉት ሰዎች ጠረጴዛ ጋር ሳይቀር በመሄድ ወዳጅ ለመምሰል ይሞክራል።
"አሁንማ ሊለይለት ነው" ይለዋል ።
ይሄንን ደግሞ ሊያም በደንብ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ " ከዴቪድ ይልቅ እናንተ በክፋቱ ጎዳና አብራችሁ የዘመታችሁ ስሜን ያጠፋችሁ ሰዎች ታስጠሉኛላችሁ መጨረሻችሁም ያሳስበኛል" ይላል ባገኘው አጋጣሚ።
ባለፈው ሳምንት ለድብድብ የደረሱበት የፀብ መነሻ
"ለመሆኑ እዚህ የምንመጣው ምን ለመከወን ነው?" ሲልም ሊያም ጠየቀ።
"ለመዝናናት" ብሎ አንዱ መለሠ
"ታዲያ ለምን አንገት ለአንገት ትተናነቃላችሁ?" ሲል ሊያም
"ይሄም ያስቀናል?" አለ ዴቪድ
"ባያስቀናም አየሩን ይረብሻል"
"የአንተ አየር በየቀኑ ነው የሚረበሸው?"
"ተውሳኮች ካሉ አዎ!መቼም አንገት ለአንገት ተያይዞ መዝናናት አላየሁም ብዬ ነው።" ሲል ዴቪድ ለዱላ ተጋብዞ ተለያዩ።
ከዚያን ቀን በኋላ ዛሬ ነው የተገናኘነው እኔና እሱ
"ቀንሽ እንዴት ነበር " አለኝ።
የተለመደና አሰልቺ መሆኑን ልነግረው አፌን ስከፍት።
"ያቺ ከመጣች ተጎልታ የምትሄደው ፕሮፌሰር ነች የሚሏት አይደለችም እንዴ?" ብለው አስተናጋጇን ሲጠይቋት ጆሮአችን ጥልቅ አለ።
ፈጥኜ አንገቱን በእጄ ወደእኔ መለስኩት።
ሊያም አፉን ከፍቶ አየኝ። አየሁት። አተኩረው ሲያዩት አይኑ ያኮራል። ሌሎቹም በሁኔታው በጣም ደንግጠዋል። እኔ ግን ደስ አለኝ። ናቅኳቸውና ወሬዬን ከሱ ጋር ቀጠልኩ። የለበስኩትን አጭር ቀሚስ ወደ ጉልበቴ እየሳብኩ "አብረኸኝ እንድትሆን እፈልጋለሁ ተዋቸው እነሱን አልኩት።
"አር ዩ ሲሪየስ?" አለኝ
"የስ አይ አም ሲሪየስ " አልኩት። ብቸኝነቴን ተበድሮ የቆመ ስለመሠለኝ ሳላስበው አይኔ እንባ አቀረረ።
"ደብል አምጪላት ለኔ ብላክ ሌብል" አለ። ውስጡ ከኔ ጋር ለመሆን የተዘጋጀ መሠለኝ።
ከዚህ ቀን በፊት አውርተን አናውቅም። ሁለት ሶስት ቀን ወንበር ለቆልኛል።
በድፍረት እጁን ያዝኩት ሰውነቴ እየተንቀጠቀጠ።
በጣም ደንግጦ አየኝ። የተናደድኩ መሠለው እንዳልሰከርኩ አውቋል። እጁን ስለያዝኩት ግራ ተጋባ። እኔ ደግሞ እጁን ስላላሸሸብኝ ተበረታትቼ "ላማክርህ የምፈልገው ነገር አለኝ" አልኩት የግንኙነታችን መሥመር እንዳይበላሽ።
"ደስ ይለኛል" አለኝ በመጠራጠር።
ከቁጥጥሬ ውጭ ሆኖ እንባዬ ተዘረገፈ። በጣም ደነገጠ እና ሶፍት አቀበለኝ። "ኩል ዳውን ኤቭሪቲንግ ኢዝ ጎነቢ ኦራይት ዶንት ዎሪ እራስሽን በእንደዚህ ያለ ሁኔታ አታሳይ አለሁ በፈለግሽው መንገድ ደግሞ ዋጋቸውን እሰጣቸዋለሁ ለነሡ አትናደጂ" አለኝ።
"ለነሱ ብዬ አይደለም እንኳን እኔ አንተም እንድትረሳቸው እፈልጋለሁ" አልኩት።
"መርሳት? መርሳት ጥሩ ነው አይደል? በተለይ መጥፎ ነገርን መርሳት? ልክ ነሽ ግን ምንም ነገር ከፈለግሽ አለሁ።" አለ
"ምንም አልፈልግም ማውራት ብቻ " አልኩት
አፌ ላይ እንደመጣ።
ግን የቱን ልንገረው ብዬ ወዲያው ስጋት ገባኝ። እኔ እኮ ያልወጣሁበት ያልወረድኩበት ምን አለ? ልጆቼን ብዬ ከእጄ የተነጠኩትን ማንነቴን? በልጆቼ የድራግ ንግድ ውስጥ መግባት ሰበብ ልጆቼን ያጣሁበትን? የቱን ነው የምነግረው ?የተመሳቀለ ህይወቴን ልጅነቴን የገበርኩበትን የስደት ህይወቴን? መጠቋቆሚያ የሆንኩበትን? በ17 ዓመቴ ከሀገሬ ወጥቼ ሀገሬ ሳልመለስ የቀረሁትን? በዚህ የተነሳ ታምሜ ሶስት አመት ከሰው ጋር ማውራት ማቆሜን ? እሶኪ የትኛውን?ከእሱ ጋር መሆን መፈለግን? የቱን? እያልኩ እራሴን ስጠይቅ አስተናጋጇ ጥብስ ይዛ መጣች።
"አዘሀል እንዴ?" አልኩት ደንግጬ
"ያስፈልገናል" አለኝ
እጄ መንቀጥቀጡን አላቆመም። አንድም የአዳፈንኩት ህይወቴ የተቆሰቆሰ ስለመሠለኝ ፤ ብቻ በረጅሙ ተንፍሼ ሳኩኝ።
"ያዢ ዛሬ በደንብ እንዝናናለን። እውነትሽን እኮ ነው ከማይመሥሉን ጋር ለምን እናባክናለን?" አለና ጣራው እስኪሰነጠቅ ሳቀ። ተከትዬው አደመኩት ሳቁን። ዲጄው ደግሞ የምወደውን ሙዚቃ ከፈተ።
"ስወድህ ውደደኝ እንካ ፍቅር በአቅሜ
ማርኮ ይግዛኝ ፍቅርህ አጠይቀኝ እድሜ
.. . . .
ስንት ነው ስንት ያየውን
አይገልፀው ፍቅር ጠቡን
. .